Saturday, January 27, 2024

የሀገራችን ታቦት ለአስማትና ለጥንቆላ ሥራ የዋለ ስለመሆኑ

የሀገራችን ታቦት ለአስማትና ለጥንቆላ ሥራ የዋለ ስለመሆኑ በመሪጌታ ጽጌ ስጦታው የተጻፈ የወጋገን መጽሐፍ እንዲህ ይለናል ተከታተሉ እመሂ ዘረገሙ ሰማየ ነጺሮሙ ምድረ ጒድጓዶሙ ታቦተ ገሲሶሙ ዕጣነ ወጊሮሙ ባሕረ በጽቢጾሙ ቆጽለ መቲሮሙ ጾመ ነቂሎሙ አስማተ ገቢሮሙ ይሠአር ሥራያቲሆሙ ለመሠርያን ኩሎሙ ዮፍታሄ በስምከ ሆልናዝር ሆልናዝር ሆልናዝር ሥራዬ ዘርዝር እምላዕለ ገብርከ ( ዓመትከ ) ትርጒም ፦ ሰማይን ተመልክተው ቢሆን ምድርንም ቆፍረው ቢሆን ታቦትን ዳሰውም ቢሆን ዕጣን አጢሰውም ቢሆን ውሃ በጥብጠውም ቢሆን ቅጠል በጥሰውም ቢሆን ቆርጠውም ቢሆን አስማት አድርገውም ቢሆን በእኔ ላይ ያደረጉት ማናቸውም ድግምት ቢሆን ሆልናዝር ሆልናዝር ሆልናዝር በተባለው ስምህ ከባርያህ ከእከሌ ላይ ብትንትን አድርግ ( መጽሐፈ ቆጵርያኖስ የዘወትር ገጽ 6 ) ልብ እንበል የመቅደሱ አገልጋዮች የሆኑት የኦርቶዶክስ ካህናት ከምንና ከምን የተዘጋጀ ድግምት እንደሚደግሙ እንመልከት :: ሰማይን በመመልከት ከዋክብትን በመቁጠር ምድርን ቆፍረው የሰው ወይንም የእንስሳትን አጥንት በማውጣት ታቦት በመዳሰስ ዕጣን በማጤስ ቅጠል በመበጠስ ሥር በመማስ የሚደረገውን አጋንንታዊ ድግምት ተመልከቱ:: እንዲሁ ብንናገረው የቤተክርስቲያን ጠላት ተደርገን በተቆጠርን ነበር :: ከራሳችን ልብ ያወጣነው ወይንም እኛ የፈጠርነው እንዳልሆነ ግን አሁን በግልጥ እየታየ ነው :: ስለ ታቦት ስለ መቅደሱ አገልግሎት ምን ያህል ክፋትም በውስጡ እንደሚደረግ የእከሌ ታቦታ ያለ መምሬ እከሌ አይያዝም ፣ አይንቀሳቀስም :: የእከሌ ታቦት እንደወጣች አልመለስም አለች የሚባለው ከምን መንፈስ እንደሆነ ልንገነዘብ ይገባል :: የዚህ መጽሐፍ ደራሲና አዘጋጅ ማለትም የቆጵርያኖስ መጽሐፍ አዘጋጅ የመቅደስ ሰው እንደሆነ ደጋሚዎችም በዚሁ አገልግሎት ውስጥ የተጠመዱ መሆናቸው የመጽሐፉ ይዘት በግልጥ ያሳያል :: የሚገርመው ድግምታቸው እንዲበጣጠስ ደጋሚ ሟርተኞች ደግሞ ታቦት ዳሰው ዕጣን አጢሰው ሥር ምሰው ቅጠል በጥሰው በሰው ላይ የሚደግሙት ራሳቸው ከታቦቱ ጋር ቅርበት ያላቸውና ታቦቱን ለመዳሰስ ዕድልና ሥልጣን ያላቸው ቀሳውስት መሆናቸው ነው :: ምን ይህ ብቻ በቅዱስ ቊርባን ማለትም በሥጋ ወደሙ ላይ ደግመው መድኃኒት አድርገው ለሴት ወይም ለወንድ መስተፋቅር የሚሰጡትስ እነርሱ አይደሉምን ? ቄሱ ቅዳሴውን እንደጨረሰ አንድ የሚለው ነገር አለው እርሱም ፦። አናምንም አንመራመርም አንማርም ያሉትን መናፍቃንን ዕጣኑን እያሸ ዕጣኑ እንደታሸ ይሻቸው አውዱ እንደተደፋ ይድፋቸው:: አውድ የተባለው ኅብስቱን የያዘው ትሪ ነው :: ታድያ ቄሱ ትሪውን እየደፋ እንዲሁ ይላል ማለት ነው :: መብራቱ እንደጠፋ ያጥፋቸው ( መብራቱ እያጠፋ ) ይላል :: ይህን ከማለት ይልቅና ምናምንቴ ድጋም ደግሞ በአጋንንታዊ ትብታብ ከማሰር ማስተማሩ መምከሩ ይበልጥ የተሻለ አይሆንምን ? ለነገሩ ሳይማሩ ምኑን ያስተምሩታል :: እንዳይማሩ እነ ደጉ ዓለም ካሣ ከተማረ ሰው ጋር አትዋል ብለዋል ሲል መሪጌታ ጽጌ ይህንን የደረሰበትን እውነት አካፍሎናል :: ሌሎችንም መረጃዎች ከአውደ ነገስት የጥንቆላ መጽሐፍ እና ከመሳሰሉት አምጥቶ ማካፈል ይቻላል :: ታድያ ታቦት ለእስራኤል ሕዝብ ብቻ ተሰጥቶ ሳለ የሌላውን ኪዳን የራስ ለማድረግ በሰሎሞን ዘመን ታቦተ ጽዮን ወደ እኛ መጣች ብሎ ይህን አሉታዊ ትርክት አሜን ብሎ መቀበል ትልቅ ስሕተት ነው :: ከዚህም ሌላ ማርያም በሰሎሞን ጊዜ ነበረችን ? ገና መች ተወለደችና ነው ታቦት የሚቀረጽላት ? ለበሬ ወለደዎች በሰጠነው መልስ መሰረት ታቦቱ በሰለሞን ዘመን መጣ ከተባለ ከሰለሞን በኋላ 16ኛ ሆኖ በነገሠው በኢዮስያስ ዘመን ታቦቱ እዚያው ኢየሩሳሌም እንደነበረ መጽሐፍቅዱሳችን ይናገራል 2ኛ ዜና 35 ፥ 3 :: ይህንን ሃሳብ በጥልቀት ስላስተማርኩበት ብዙ አልሄድበትም :: ያነሳሁበት ጉዳይ ግን በቲዎሎጂ ማስተርሱን የሰራው ዶክተር ወዳጄነህ የበሬ ወለደ ታሪክ ተናጋሪዎችን ወሬ ሰምቶ ታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ መጥታለች በዓይኔ በብረቱ አይቻለሁ አስራቴንም ለእርስዋ መስጠት ጀምሬያለሁ ተቀላቀሉኝ አንድ ላይ እንሁን በማለት ጠቅላይ ሚኒስቴርያችንን ሳይቀር አክሱም ጽዮን ሄደው ቢባረኩ በመንግስትዎ ውጤታማ ይሆናሉ ድል ይቀናዎታል ማለቱ ከእርሱ እውቀትና የትምህርት ደረጃ ጋር አብሮ የማይሄድ በመሆኑ ጉዳዩ ገርሞኝና ድንቅ ብሎኝ ነው :: ይህ የዶክተር ወዳጄነህ አካሄዱ ደግሞ አሁን ላይ ባለ ነገሩ አቋሜና መብቴ ነው ተጠምቄ የኦርቶዶክስ አባል ብሆንስ ማን ይከለክለኛል ? ሲል ዘርዘር አድርጎ በተናገረው ጉዳይ ላይ አላዋቂ አሰኝቶታል :: ሰዎችም በብዙ ታዝበውታል :: የኦርቶዶክስ አባል መሆን ከፈለገ ጥንቱኑስ ማን ከለከለው ? ሲጀመርስ የወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት ሰባኪና የእምነቱ አካል ማን ሁንልኝ አለው ? እኔ ሲገባኝ የግዴታ እምነትም ሆነ አገልግሎት የሰጠን የለም :: ስናምን ወደን ገብቶናል ብለን ነው ያመነው :: ስናገለግልም ወደን እና ገብቶናል ብለን ነው የምናገለግለው :: ከዚህ ውጪ ከጀርባችን የቆመ አስገዳጅ ኃይል ለማናችንም የለንም :: ወዳነሳነው መሠረታዊው ጉዳይ ስመለስ እኛ ኢትዮጵያውያን አሕዛባውያን ስለሆንን ታቦት የለንም :: ታድያ ይሕንን ያወቁ ብልጥና ነጋዴ ጠንቋይ ካህናቶች ናቸው ታቦቱ በሰለሞን ዘመን ወደ እኛ መጥቶአል የሚለውን የውሸት ትርክት ይዘው ታቦቱ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳለ በመቁጠርና አውደ ነገሥታቸውንም በመድገም ጥንቆላቸውን የሚያጧጡፉት :: ታድያ ታቦቱ ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣ ሳይሆን እንዳልመጣ ወይም እንደሌለ ያመኑ ጠንቋይ ካህናት ናቸው እነዚህ ካህናት :: ስለዚህ ታቦቱ በአሁኑ ሰዓት ለእነርሱ የመክተፍያ ያህል ስለሆነ ይህን ተላላና ምስኪን ሕዝብ ታቦት በሰለሞን ጊዜ የመጣልህ ክብርህ ነው በማለት በታቦቱ ጀርባ ይህንኑ ከላይ የዘረዘርኩትን ጥንቆላ ያስፋፋሉ:: አያይዘውም የእንጀራቸው ጉዳይ ነውና ታቦትን አክብር ባታከብር የኦዛ ስብራት ያገኝሃል ፣ ትቀሰፋለህ በማለት ሕዝብን ማስፈራራታቸው ሳያንሳቸው ፣ በታቦቱ ስም ደግሞ ሆዳቸውን ሊሞሉ ለታቦቱ ክብርና ታቦቱ ሄዶ ወደ ማደርያው እንዲገባ ደም ይፍሰስለት በግ ፣ በሬ ይታረድለት እያሉ ታቦት ወጥቶአለ በተባለበት ቦታ ሁሉ ይወተውታሉ :: ይህንን የሚያደርጉት ግን ጥቅማቸው እንዳይቀርባቸውና የስዕለት ገንዘብ ለመብላት ሲሉ ፣ ለሆዳቸውም ጭምር ነው :: ደም ሲፈስለት ደግሞ ይህንኑ የጠንቋይ ቀሳውስቱን አጀንዳ ለማስፈጸም በዚያው ልክ በታቦቱ ላይ ያለው የጥንቆላ መንፈስና አደራረግ እግረ መንገዱን ይገለጣል :: ታድያ ታቦቱን እንዳይቀርቡት የኦዛ ስብራት ሕዝቡን የሚያገኝ ከሆነ ታቦቱን እየዳሰሱ የሚጠነቁሉትን እነዚሁኑ ጠንቋዮች ለምን ቀድሞ አላገኛቸውም ? እነርሱ ላይ ሲሆን ታቦቱ ይደክማል ማለት ነውን ? መልሱን ለእናንተ ለአንባቢዎች እተዋለሁ :: ስለዚህ ከዚህ በኋላ መወሻሸትም ሆነ የውሸት ማስፈራራት አያስፈልግም :: ታቦትን ለአስማትና ለጥንቆላ ሥራ መጠቀምያ እናድርግ ካላልን በስተቀር ታቦት እኛ ኢትዮጵያውያን ጋር የለም :: አይኖረንምም :: አሁን ላይ ያለ ታቦት በመጎናጸፍያ ተሸፍኖ ነገሠ እልል በሉለት ተብሎ በሬና በግ ቢታረድለት ፣ አልፎም ደግም የጠንቋዮች መጠቀምያ ሊሆን እየተዳሰሰና እጣን እየተጬሰ ቢጠነቆልበትም ምናልባትም አጋንንቱ የሚሳብበት ታቦት በኢየሱስ ብቸኛ አዳኝነት ያላመኑትን ሰዎች ይዋጋ ካልሆነ በስተቀር ክብሩ በኢየሱስ ክርስቶስ የተተካ በመሆኑ እኛ ላይ የኦዛ ስብራት አያመጣም:: ተሸክሞ ወጥቶም ለሆድ መሙያ የሚሆን የበሬና የበግ እርድ ከሚያስገኝ በቀር ፍጹም በሬ ወለደ ነውና ስለተሸከምነው ብቻ የጦርነት ድል አይሰጠንም :: ይሄ ሁሉ የነ ምሕረተ አብና የነዘበነ ለጥቅምና ለእንጀራ መብያ የሆነ የውሸት ዲስኩር ነው :: አሁን ደግም አስራት ሰጪውና ታቦተ ጽዮንን ተሳለሚው ዶክተር ወዳጀነህ ተጨምሮበታል ፣ እግዚአብሔር ይራራላቸው ፣ ይድረስላቸውም ነው የሚባለው :: ይሁን እንጂ አሁን ላይ ተነስቶ ዶክተር ወዳጄነህ እንዳደረገው ሰዎችን ወደ ታቦት መምራት ወዴት መምራት እንደሆነ ለሁላችሁም ግልጽ የሆነ ይመስለኛል :: አሁን ሃሳቤን ጨርሼአለሁ መልዕክቴንም በዚሁ እጠቀልላለሁ :: በዚህ መልዕክት ተጠቀሙ :: ለሌሎችም አድርሱልኝ ተባረኩ ሻሎም አባ ዮናስ ጌታነህ ሐዋርያዊ አገልጋይ ከኦርቶዶክስ ተሃድሶ