Tuesday, July 13, 2021

ጥንቆላ - በሀገራችን ፣ በቤተ ክርስቲያናቸን እንዲሁም
በእያንዳንዳችን ላይ ሊኖረው የሚችለው ተጽዕኖ



ጥንቆላ - በሀገራችን ፣ በቤተ ክርስቲያናቸን እንዲሁም
በእያንዳንዳችን ላይ ሊኖረው የሚችለው ተጽዕኖ
Read in PDF
ራሳችንን ከጥንቆላ ስራዎች ለመጠበቅ ወይንም ሳናውቅ
የጥንቆላ ስራዎች ተባባሪ ከመሆን ለመዳን ስለ ሀገራችን
የጥንቆላ ዘዴዎች መጠነኛ ግንዛቤ ሊኖረን ይገባል። ጠንቋይ
ማለት ጠንቅ ዋይ ወይም ጠንቀኛ ማለት ነው። በሀገራችን
ሁለት ዓይነት የጠንቋይ አይነቶች አሉ። አንደኛው ወገን ባለ ዛር፣
ባለ አውሌ (ውቃቤ) የሆኑትን ሲያካትት ሁለተኛው ወገን ደግሞ
ደብተራ የሚባሉትን ያካትታል።
ባለ ዛር ወይንም ባለ ውቃቤዎች
አውሌ ወይም ዛር የሚባሉት በሰው ላይ ሰፍረው አምልኮን
ለራሳቸው የሚወስዱ የአጋንንት ወገን ናቸው። ባለ አውሌዎች
በመላው ኢትዮጵያ ይገኛሉ። በኦሮሞው፣ በአማራው፣ በጉራጌው
ወዘተ በየትኛውም ብሔር ብሔረ ሰብእ ዘንድ በብዛት አሉ።
ብዙዎቹ ሃይማኖታቸው እስልምና ወይም ኦርቶዶክስ ክርስቲያን
እንደሆኑ ይናገራሉ። ብዙውን ጊዜ አማኞች ለመምሰል የአላህን
ወይም የእግዚአብሔርን ስም ያነሳሉ። እንዲህ የሚያደርጉት
ብዙዎች ደንበኞቻቸው ከእስልምና ወይም ከክርስትና የመጡ
ስለሆኑ ይመስላል። ኢየሱስ የሚለውን ስም ግን ተሳስተውም
እንኳ አይጠሩትም።
«እስላም» ነኝ የሚለው ባለውቃቤም ሆነ «ክርስቲያን» ነኝ
የሚለው ባለ ውቃቤ ገብርኤልን ሚካኤልን እና አቡየ ገብረ
መንፈስ ቅዱስን ይወዳሉ። በየዓመቱ ዝክራቸውን ይዘክራሉ ቤተ
ክርስቲያናቸውን ይሠራሉ በየቤታቸውም ስእሎቻቸውን
አንጠልጥለው እጣን ያሳጥናሉ፤ በበአላቸው ቀን ጃንጥላ፤ በሬና
ጊደር የመሳሰሉ ስእቶችን ያደርጋሉ። ይህን የሚያደርጉት
ክርስቲያን ባለውቃቤዎች ብቻ አይደሉም፤ እስላሞችም ጭምር
ናቸው እንጂ። እኛ ካህናቱም ይህን እያወቅን መባቸውን
(ስዕለታቸውን) እልል ብለን እንቀበላቸዋለን። በቁልቢ ገብርኤል
ከሚገኘው መባእ ውስጥ አብዛኛውን የሚሰጡት የእስላምናና
ክርስቲያን ባለውቃቤዎች ናቸው። በቁልቢ ገብርኤል ከመተካቱ
በፊት ባለ አውሌ ያሟርትበት የነበረ ሥፍራ ነበር ሲባል
ሰምቻለሁ። ዛሬም በስፍራው ባለውቃቤዎች አይታጡም። ባለ
ውቃቤዎች በሚካኤልና በገብርኤል ቀን ደመቅ ያለ ዘፈን
አላቸው ዝክርም ይዘክራሉ። ጽድቅን ለማግኘት ይሆን? የነሱ
ደግሞ እስከ ስንት ትውልድ ይማር ይሆን? ለምሳሌ ምእራብ
ሽዋ ውስጥ የሚገኘው የሙገሩ ታዋቂ ጠንቋይ የሚካኤልን ቤተ
ክርስቲያን አሠርቶ ህዳር ሚካኤልን ሞቅ ባለ ድግስ ይዘክራል።
በዚያ ቀን ከአዲስ አበባ ወደ ባለ ውቃቤው የሚጓዘው ሕዝብ
እጅግ ብዙ ነው። በጎጃም አዲስ ቅዳም ውስጥ የሚገኘው
ታዋቂ ጠንቋይ የገብርኤልን ቤተ ክርስቲያን አሠርቷል። በወሎ
ያለው ታዋቂ ባለዛር ግን መስጊድ አሰርቷል። ታዋቂ ጠንቋዮችን
ለምሳሌ ያህል ጠቀስሁ እንጂ ሁሉም ባለውቃቤ የራሱ የሆነ
ታቦት አለው። ነገር ግን በሚካኤልና በገብርኤል ስም
የሚነግደው ያ ጥንተ ጠላታችን ሰይጣን እንደሆነ ጥርጥር
የለውም።
ዛሩ በነርሱ ላይ የሚወርደው በልዩ ልዩ አምልኮ ሲለማመጡት
ነው። ቡና ይፈላለታል ዶሮ ወይም በግ ይታረድለታል፤ ስግደት
ይቀርብለታል፤ ዘፈን ይዘፈንለታል፤ አታሞና ከበሮ ይመታለታል።
በዚህ ጊዜ ባለውቃቤው ከመጋረጃ ውስጥ ሆኖ ያጓራል። በዚህ
ጊዜ መንፈሱ ወረደ ይባልና እልልታ ይደረጋል። እርሱም
የሚረግመውን ይረግማል የሚመርቀውን ይመርቃል። ከዚያም
ለማስጠንቆል የመጡ ደንበኞቹ ሁሉ በተራ እየሰገዱ እጣ
ፈንታቸውን ይጠይቃሉ የተጣሉትን ያስረግማሉ። እባክህ አትርሳኝ
እያሉ ይማጸናሉ። በማግስቱ ደግሞ በማርያም ስእል ፊት
ወድቀው እባክሽ አማልጅኝ እያሉ ይጸልያሉ። ወይ ያላረፈች
ነፍስ!
ደብተራ
ደብተራ ማለት ድንኳን ማለት ነው። ደብተራ የሚለው ስያሜ
ለቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች የተሰጠው በዘርዓ ያዕቆብ ዘመን
ነው ይባላል። በድንኳን ውስጥ በጽሑፍና በድርሰት በማህሌት
የሚያገልግሉ የዘርዓ ያዕቆብ ሰራተኞች ካህናተ ደብተራ ይባሉ
ነበር። በድንኳን ውስጥ ስለሚኖሩ ስማቸው ደብተራ ተብሎ
ይጠራ ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በማህሌት ክፍለ አገልግሎት
የሚመሰማሩ አገልጋዮች ደብተራ ይባላሉ። ሚስታቸው
የሞተችባቸው ቄሶች ወደ መቅደስ ገብተው መቀደስ አይችሉም፤
ቅኔ ማህሌት ገብተው ግን ማገልገል ይችላሉ። በዚህ ምክንያት
ደብተራ ይባላሉ።
የቤተ ክርስቲያን ትምህርት የጸነነባቸው ማለት ቅኔው
ያልገባቸው፤ ዜማው ያልተቃኘላቸው ሰዎች በአቋራጭ ዘወር
ብለው የሰሎሞን ጥበብ የሚሉትን ጥንቆላ ይማራሉ። ትምህርቱ
የገባቸውም አንዳንዶች ጥንቆላውን ይማሩታል። በጥንቆላ
ትምህርት የታወቀ መሪጌታ፣ ቄስ ወይም ገበሬ ያልተማረ እንኳ
ቢሆን ደብተራ ይባላል።
የደብተራ ጥንቆላ ከድግምት ጋር የተያያዘ ነው። ድግምቱ
ትርግሙ የማይታወቅ ስም ቋንቋና አሠራር አለው። ሆኖም
ሥራው የሚሠራው በአጋንንት ኃይል ነው። ከአጋንንት ጋር ቃል
ኪዳን በማድረግ ከፍተኛ መተቶችን ይሠራሉ። ብዙ ጊዜ
ደብተራዎች ቃል ኪዳን ለማድረግ የሚመርጧቸው የአጋንንት
አለቆች በደብተራዎች አጠራር የሚከተሉት ታዋቂዎች ናቸው።
አየረ ጴጥሮስ፦ አየረ ጴጥሮስ የሚባለው ሰውን ለመግደል፤
ለማፍዘዝ፤ ለማሳበድ፤ የሚዋረሱት አደገኛ የአየር ጋኔን ነው።
አየረ ጴጥሮስን የተዋረሱ ደብትራዎች ሴትና ሽቱ ይወዳሉ።
ገንዘብ ያገኛሉ ግን አይበረክትላቸውም። በየጊዜው ለጋኔኑ ደም
የሚገብሩ ሲሆን ቤተ ክርስቲያን ገብተው ማገልገል በጣም
ይወዳሉ።
አፈ ሕጻን፦ አፈ ሕጻን የሚባለው ደግሞ የምድር ጋኔን ነው።
ልክስክስ ደካማ ጋኔን ሲሆን በሰው ላይ የሚፈጽመው ተንኮል
ግን ከባድ ነው። በቡና በአረቄና በጠላ የሚሳብ ነው፤ አፈ ሕጻን
የተባለበት ምክንያት በሕጻን ልጅ የሚሳብና በሕጻኑ አንደበት
የሚናገር ስለሆነ ነው። ጋኔን የተሳበበት ሕጻን የኋላ የኋላ እብድ
ሊሆን ወይም የአእምሮ ዝግመት ሊያጋጥመው ይችላል።
ስሙ ለአብ፦ ይህ ጋኔን ለአቃቤ ርእስ ለሀብትና ለሥልጣን
የሚዋረሱት ሰይጣን ነው። ባለ ሥልጣን ባለሀብት ሆነው
ትዕቢተኞች ይሆናሉ፤ ጠባያቸው ከማንም ጋር አይስማማም።
ይህን ጋኔን የተዋረሱ ሰዎች እጅግ አመንዝራዎች ናቸው። በዚህ
ጋኔን የሚገለገሉ ጠንቋዮችም ሆኑ አስጠንቋዮች በብዛት
ታንቀው ይሞታሉ። ወይም በድንገት ሞተው ይገኛሉ። በነገራችን
ላይ ደብተራዎች ስሙን እየቀያየሩ ይጥሩት እንጂ ያው አንዱ
ዲያብሎስ ነው።
ደብተራዎች የተለያየ ዓይነት ናቸው። ሰይጣንን ሳይዋረሱ
በድግምትና በሟርት የሚሠሩ፤ ሰይጣንን ተዋርሰው [ቃልኪዳን
ገብተው] የሚሠሩ፤ መናፍስትን የሚጠሩ፤ ምሕሳበ ቅዱሳን
የሚደግሙ፤ መልክአ ሳጥናኤል ብቻ በመድገም የፈለጉትን
የሚያደርጉ አሉ። እንዲህ ዓይነት ሥራ አይሠራም ሰይጣንም
ይህን ያህል አይሰራም የምትሉ አንባብያን ካላችሁ ሰይጣንም
የሚፈልገው እንዲህ አይነቱን መዘናጋት እንደሆነ
እንድትረዱትና እንድታስቡበት እጠይቃለሁ።
በመጽሐፍ ቅዱስ ጠንቋዮችና መናፍስት ጠሪዎች የተወገዙ
ናቸው።
«ወደ መናፍስት ጠሪዎችና ወደ ጠንቋዮች አትሂዱ
እንዳትረክሱባቸውም አትፈልጉአቸው እኔ እግዚአብሔር
አምላካችሁ ነኝ» ዘሌ 19፥31።
«መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን በሚከተል በሥራቸውም
በሚያመነዝር በዚያ ሰው ላይ ፊቴን አከብዳለሁ ከሕዝቡም
መካከል ለይቼ አጠፋዋለሁ» ዘሌ 20፥6።
«ወንድ ወይም ሴት መናፍስትን ቢጠሩ ወይም ጠንቋዮች ቢሆኑ
ፈጽመው ይገደሉ በድንጋይ ይውገሯቸው በማቸው በላያቸው
ነው» ዘሌ 20፥27።
«አስማተኛም መተተኛም፣በድግምት የሚጠነቁልም፣
መናፍስትንም የሚጠራ፣ ጠንቋይም፣ ሙታን ሳቢም፣ ባንተ ዘንድ
አይገኝ» ዘዳ 18፥11።
ከላይ እንደዘረዘርሁት አስማተኛ ማለት ትርጉማቸው የማይታውቁ
ስሞችን መጥራት ማለት ነው። እንዲህ ዓይነቱን አስማት
ለማየት «መልክአ ራጉኤል» እየተባለ የሚጠራውን በተስፋ ገብረ
ሥላሴ ማተሚያ ቤት የታተመውን የጸሎት መጽሐፍ እንደ ምሳሌ
ያህል መመልከት ነው።
መተት ማለት ማስመስል ማለት ነው። በአይን ላይ የሚደገም
አስማት ነው። ለምሳሌ ኢያኔስና እያንበሬስ የተባሉ የግብጽ
ጠንቋዮች መተት አዋቂዎች ነበሩ ዘጸ 7፥11።
ድግምት ደግሞ ፍለጠው ቁረጠው እያሉ በአጋንንት ስም
መራገም ነው። ድርሳነ ሚካኤል በጥቂቱ ይህ ዓይነቱ ድግምት
ይገኝበታል፤ የሕዳር ሚካኤል የሚነበበውን ይመልከቱ።
መናፍስትን መጥራት ከላይ እንዳየነው የተለያዩ አጋንንትን
መጥራት ሲሆን በቃል ኪዳን ተዋርሰው የታዘዙትን ሁሉ
ያደርጋሉ።
ሙታን ሳቢ፦ ይህ ጥንቆላ በአገራችን ደብተራዎች ቋንቋ
ምህሳበ ቅዱሳን ይባላል። የሞቱ ቅዱሳንን ለመጥራት
የሚያገለግል ድግምት ነው። እንዲህ አይነቱን አስማት
ባሕታውያን እየተባሉ የሚጠሩ ደብተራዎች አዘውትረው
ይጠቀሙበታል። ሆኖም ግን በሙታን ስም የሚመጣው ያው
የታወቀው ጠላታችን መሆኑ አያጠያይቅም። ሙታንን የሚስቡ
ሰዎች እራሳቸውን ከሰው አግልለው መኖር ይመቻቸዋል።
በመጽሐፍ ቅዱስ ሙታንን መጥራት የቻሉ ጠንቋዮች እንደነበሩ
ተጽፏል 1 ሳሙ 28፥9።
ደስ የሚያሰኘው ነገር
እነዚህ በሰማይና በምድር ያሉ ኃይላት በባለ ውቃቤም ሆነ
በደብተራ ስም ይምጡ እንጂ፤ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ
ስም ይንበረከካሉ። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስም አጋንንት
የማይቋቋሙት ስም ነው። «ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም
ሰጠው ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ
በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር
አብ ክብር ኢየሱስም ጌታ እንደሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው» ፊልጵ
2፥10-11። ሟርትም አስማትም በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው
ስሙን በሚጠሩ ላይ ፈጽሞ አይሰራም። ወደ እግዚአብሔር
የተጠጉ ሁሉ ከሰይጣን ወጥመድ ያመልጣሉ።
«በልዑል መጠጊያ የሚኖር ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ
ያድራል።
እግዚአብሔርን፦ አንተ መታመኛዬ ነህ እለዋለሁ አምላኬና
መሸሸጊያዬ ነው፥ በእርሱም እታመናለሁ።
በላባዎቹ ይጋርድሃል፥ በክንፎቹም በታች ትተማመናለህ እውነት
እንደ ጋሻ ይከብብሃል።
በጨለማ ከሚሄድ ክፉ ነገር፥ ከአደጋና ከቀትር ጋኔን አትፈራም።
በአጠገብህ ሺህ በቀኝህም አሥር ሺህ ይወድቃሉ ወደ አንተ
ግን አይቀርብም።
አቤቱ፥ አንተ ተስፋዬ ነህና ልዑልን መጠጊያህ አደረግህ።
ክፉ ነገር ወደ አንተ አይቀርብም፥ መቅሠፍትም ወደ ቤትህ
አይገባም።
በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ
ያዝዛቸዋልና
እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል።
በተኵላና በእባብ ላይ ትጫማለህ አንበሳውንና ዘንዶውን
ትረግጣለህ።
በእኔ ተማምኖአልና አስጥለዋለሁ ስሜንም አውቆአልና
እጋርደዋለሁ»። መዝ 90 [91]
አማላክችን ከጨላማው ስልጣን አድኖ ወደ መንግሥቱ
አፍልሶናል ቈላ 1፥13። እባቡን እና ጊንጡን እንረግጥ ዘንድ
ሥልጣን ሰጥቶናል ሉቃ 10፥19።ጠላታችን ከእግራችን በታች
ፈጥኖ የሚቀጠቅጠው እርሱ ጠላቶቹን ከግሮቹ በታችን
የረገጣቸው ዛሬም በደሙ ይሸፍነናል። ሮሜ16፥20።
ክርስቲያኖች በዚህ እጅግ ደስ ልትሰኙ ይገባል።
ኢትዮጵያዊ ወገናችንን ለመርዳት የምንፈልግ ሁሉ ወንጌልን
እንስበክ፤ ለነጻነት፤ ለልማት፤ ለዲሞክራሲ፤ ለፍትሕ እንታገል።
ሕዝባችን በመናፍስት ጠሪዎች እጅ ስለወደቀ በረከት ርቆት
በችግር ላይ ይገኛል። ነጻ የሚያወጣን የይሁዳ አንበሳ የናዝሬቱ
ኢየሱስ ነው።
በቀረውስ በጌታና በኃይሉ ችሎት የበረታችሁ ሁኑ የዲያብሎስን
ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን እቃ ጦር
ሁሉ ልበሱ መጋደላችን ከሥጋና ከደም ጋር አይደለምና
ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዥዎች
ጋር በሰማያዊም ሥፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሰራዊት ጋር
ነው እንጂ ኤፌ 6፥10-13።

No comments:

Post a Comment