Wednesday, March 9, 2022
+++ምሥጢረ ሃይማኖት+++
ምሥጢር ማለት በዓይን የማይታይ በቃላት የማይገለፅ ከአእምሮ በላይ የሆነ ማለት ነው፣ሃይማኖት ማለትም ማመን ማለት ነው ፣ ምሥጢረ ሃይማኖት ማለት የሃይማኖት ወይም የማመን ምሥጢር ማለት ነው፣ ይህም ምሥጢር ምሥጢረ ሥላሴ ወይም የሦስትነት ምሥጢር ነው።
ምንም እንኳን በቤተ ክርስቲያን ትምህርት አምስት አዕማደ ምሥጢራት፣ ሰባት ምሥጢራተ ቤተ ክር ስቲያን ቢኖሩም ቅሉ መነሻቸውና መድረሻቸው ግን ምሥጢረ ሥላሴ ነው፣ ምሥጢረ ሥላሴ ሲተነተን ሲዘረዘር ሲብራራና ሲገለጥ ሌሎቹ ምሥጢራት ይወለዳሉ ፣ ስለዚህም ሌሎቹ ምሥጢራት የምሥጢረ ሥላሴ ውላጆች ናቸው። ይህም የሆነበት ዋና ምክንያት ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ ከድንግል መወለዱ ነው፣ እርሱ በሥጋ በምድራችን ሲወለድ፣ በእኛ ቋንቋ ሲናገር እንደኛ ሲበላ ሲጠጣ ሲታይ፣ ሲደክም ሲራብ ሲጠማ ሲጎሳቈል ስናየው ምሥጢራትን አየን፣ የሰማዩን ተረከልን፣የአባቱን ክብር የባህርይ ሕይወቱን የመንፈስ ቅዱስን ክብር አየንበት ፣ በመጠናችን አንጸባረቀልን፣ "ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እንዴትስ አንተ። አብን አሳየን ትላለህ?" እንዳለ ዮሐ14 : 9።
ቅዱስ ጳውሎስም፦
"እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ" ብሏል፣ ዕብ 1÷3
የተሰወረውን እንደዓቅማችን ገለጠልን።"ምሥጢሩ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው። የተገለጠው ግን ለዘላለሙ ለእኛና ለልጆቻችንም ነው" ዘዳ 29÷29፣ሐዋ 2÷38፣ ሉቃ 10÷21፣1ኛ ዮሐ 1÷2፣ኤፌ 3÷3 ፣3÷8፣ 1ኛ ጴጥ 1÷19—21
ምሥጢረ ሥጋዌን ስንመረምር ደግሞ ሌሎቹ ምሥጢራት ተገለጡልን፣ ምሥጢረ ጥምቀትን ሰው ሆኖ ሥጋ ለብሶ በመስቀል ተሰቅሎ ከጎኑ ባፈሰሰው ቅዱስ ውሃ አየነው፣ ምሥጢረ ቊርባንን በዕለተ ሐሙስ ሠርቶ አሳየን፣ ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በርሠ መቃብር አድሮ በሦስተኛው ቀን ተነስቶ አሳየን።
ሌሎቹ የአገልግሎት ምሥጢራት ደግሞ ከምሥጢረ ጥምቀት ተወለዱ(ክህነት፣ ተክሊል፣ ንስሐ፣ሜሮን፣ቀንዲል)።
ይህንንም ምሥጢር ራሱ ባለቤቱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ አስተምሯቸዋል፣ ለሊቁ ለኒቆዲሞስም በስፋትና በጥልቀት ለብቻው በረቀቀ አገላለጥ ያስተማረውን ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ መዝግቦታል ዮሐ 3÷1—22፡፡
በነዚህ መሠረትነት ምሥጢረ ሥላሴን እንመረምራለን፣ እንማራለን፣ እንደ ዓቅማችን ሀልዎተ እግዚአብሔርን እንናገራለን ይህም ምሥጢረ ሃይማኖት በመባል ይጠራል።
ሃይማኖት እግዚአብሔርን ከምንመረምርበት በተጨማሪ መንፈሳዊነታችንን የምናዳብርበት እንደመላእክት መኖርን የምንለማመድበት ሥርዓተ አምልኮ ነው። መሠረታዊ የቃሉ ትርጉም እምነት ከሚለው ቃል የተሻገረና ያለፈ ትርጉም የሚሰጠውም በዚህ ምክንያት ነው፣ ሃይማኖት የማይታየውን እግዚአብሔርን እንዳየነው እንደሰማነው እንደደዳሰስነውና እንደጨበጥነው አድርገን የምንናገርበት ትልቅ መሳሪያችን ነው፣ ከዚህም በላይ ሰዎች ሁሉ ልንግባባበት የሚገባን የነፍስ ቋንቋ ነው።
ቅኝቶቹም፦
• ለባዊነት
• ነባቢነትና
• ሕያውነት ናቸው፡፡
በዚህ ቋንቋ ነው ከመላእክት ጋር የምናወራው የምንግባባውም፣ ዓለማችን ይህን ቋንቋ አያውቅም አይረዳም ፣ በዚህ ምክንያት ሃይማኖታውያን ስንሆን ዓለም ታሳድደናለች ትገፋናለች ትገርፈናለች ታሰቃየናለች ።
ከጥንት ጀምሮ በዚህች ሃይማኖት ብዙዎች ደማቸውን አፍሰውባታል፣ አጥንታቸውን ከስክሰውባታል፣ ሕይወታቸውን ከፍለውባታል ይህ የሃይማኖት ምሥጢር ነው። ሃይማኖት አንዲት ናት የምንልበት ምሥጢርም ከዚህ በመነሣት ነው፡፡
"አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት" እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ ኤፌ 4 : 5 ።
የሰማያውያን ሁሉ ቋንቋ ፣ የመላእክትና የሰዎች (የክርስቲያኖች) ኅብረት (ጉባኤ) መግባቢያ ይህች አንዲቷ የእኛ ሃይማኖት ብቻ ናት፣ ይህችም አንድ ጌታ(አንድ እግዚአብሔር) ያላት ናት ፣ ከመላእክት ጋር የተግባባነው፣ ዓለም ከጠላቸውና ካሰደዳቸው ቅዱሳን ጋር አውርተን የምንግባባውም ለዚህ ነው፣ ይህች ሃይማኖት ስላለችን፣ ሦስት መቶ አስራ ስምንቱ ሊቃውንትም ይህችን ሃይማኖት "ኦርቶዶክስ" (ርትዕት ሃይማኖት—የቀናች የተስተካከለች ሃይማኖት) ብለው መሰየማቸው በዚህ ምክንያት ነው፣ ከሰማይ የተሰጠችን ወደሰማያት የምንሄድባት ማለፊያ መሻገሪያ መንገድ፣ መግባቢያ፣ ማመስገኛ ለዘለዓለም መኖሪያ መናገሪያ ቋንቋችን ስለሆነች ነው፣ ይህችውም ጠባብ ናት ጥቂቶች ብቻ ይገቡባታል፣ ዓለመ ሥጋን ፈቃደ ሥጋን አሸንፈው ይገቡባታል፣ማቴ 7:13 የዚህች ቋንቋ ጥግ ምሥጢር ምሥጢረ ሥላሴ ነው።
ሥላሴን ለማድነቅ፣ ለማመስገን ፣ ለማምለክ ፣ በዓቅም ለመመርመር ፣ ስለ ሥላሴ ለሌሎች ለመናገር ሃይማኖት ያስፈልጋል፣ ራሱ ምሥጢሩ በሃይማኖት ቋንቋነት ካልሆነ አይገለጽም ፣ ሃይማኖት ሌላ ቀመር የለውም፣ ቀመሩ ማመን ነው!!! እውነተኛነቱ የሚረጋገጠውም በማመን ነው! ሃይማኖት እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ ያሰቀመጠው ኃይል ነው ፣ ይሄን ስንረዳ ዓለማችን ነዳጅ ቆፍራ ለማውጣት ከምታደርገው ጥረት በላይ እኛ እግዚአብሔርን ለማግኘት ጥረት እናደርጋለን፣ እንተጋለን፣ ይህ በውስጣችን ያለው ኃይል ሲቀጣጠል በዓለም የሚቀጣጠለውን እሳት ፣ በጋን ውስጥ እንደ ክረምት ነጎድጓድ የሚፈላውን ውሃ እንረሳለን፣ ስለሃይማኖታችን ወደመከራው ለመግባት እንቸኩላለን፣ ምክንያቱም በውጪ ከሚቃጠለው ኃይል በላይ እኛ ውስጥ የሚቃጠለው(ሃይማኖት) ስለሚበልጥ።
አባቶቻችን ነቢያት ከዚህ ዓለም ስላልሆኑና በውስጣቸው ያለው አግዚአብሔርን የማምለክ ዓቅም ከዓለም ረብኅ ስለበለጠባቸው ከዓለም ወጥተው ተቅበዝብዘዋል " ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ" ዕብራውያን 11 : 38፡፡
ሐዋርያትም እንዲሁ በእሳትና በስለት አልፈዋል፣ ይህም በውስጣቸው በሚነደውና በሚቀጣጠለው አምልኮተ እግዚአብሔር ምክንያት ነው፣ይህም ሕይወትን እስከማስከፈል ዓቅም ያለው የኃይል ቋንቋ ነው።
በዚህ ምክንያት ሃይማኖት ራሱ ምሥጢር ተብሎ ይጠራል። የምሥጢርነቱ ማብቂያውና ጥጉ፣ መድረሻውና መጨረሻውም ምሥጢረ ሥላሴ ነው። ይህንንም ይዞ ሊቁ እንዲህ አለ:—"ሃይማኖት እንተ እምኀበ አብ ተወጥነት ወኀበ ወልድ ታበጽሕ ወበኀበ መንፈስ ቅዱስ ትትፌጸም"
"ሃይማኖት በአብ ተጀምራ ወደ ወልድ ታደርሳለች፣ በመንፈስ ቅዱስም ትፈጸማለች" ሃይ አበው።
ይህ የሊቁ አነጋገር ብዙ ምሥጢራትን ያቀፈ ከሀገር ከዓለም የሚሰፋ ቃል ነው፣ አብ ማለት አባት፣ ወልድ ማለት ልጅ፣ መንፈስ ቅዱስ ማለት ቅዱስ እስትንፋስ(ሕይወት) ማለት ነው ፣ ሃይማኖት የሚጀምረው አብን አባት በማለት ሲሆን አባትነቱ ለማን ነው? በሚለው ጥያቄ ደግሞ ለ"ወልድ" ወደሚለው እንደርሳለን ፣ አባት(አብ) እና ልጅ(ወልድ) እንዴት ይኖራሉ? የሚለው ጥያቄ ደግሞ መልሱ ወደ መንፈስ ቅዱስ ይወስደናል ፣ ይህም ማለት እስትንፋሳቸው መንፈስ ቅዱስ ነው የሚል የመጨረሻ መልስ እናገኛለን፣ ይህ አኳዃን እነሱ የሚገለጡበት አኗኗር ነው! ይህ ደግሞ ለእኛ ምን ጥቅም አለው ወደሚለው እንምጣ! የእኛ ተፈጥሮ ሱታፌ—ሥላሴ ያለው ነው፣ በባህርይ ሳይሆን በጸጋ ከሥላሴ ጋር አንድነት እንዲኖረን የተፈጠርን ነን።
ሊቁ ቅዱስ ዲዮናስዮስ ፦
"ወንበርህ በአስማተ ቅድስት ሥላሴ ዘውእቱ እምነትነ" (የሦስቱን ስም በመጥራት አዋቂዎች እንሆናለን፣ ይኸውም እምነታችን ነው) እንዳለ።
አብ አካላዊ ልብ ነው፣ ወልድ አካላዊ ቃል ነው፣ መንፈስ ቅዱስ አካላዊ ሕይወት ነው። በእኛ በሰዎች ውስጥ በአካላዊነት ሳይሆን በዝርውነት የሚገኙ ለባዊነት፣ነባቢነትና ሕያውነት የነፍሳችን ባህርያት ናቸው ፣ እነዚህም ከሥላሴ ያለንን ሱታፌ ያሳያሉ።በለባዊነታችን አብን፣ በነባቢነታችን ወልድን፣ በሕያውነታችን መንፈስ ቅዱስን እንመስላለን!
"እግዚአብሔርም አለ። ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ።:" በማለት ሙሴ የጻፈውም ይህንን ምሥጢር ነው፣ ዘፍ1 : 26።
አዳም ሲፈጠር እነዚህን አሟልቶ ፣ መልኩና አካሉ ምሉእነት ሳይኖረው ውሱን ሆኖ ተፈጠረ ፣ ይህንን መልክና አካል ፣ ጠባዕይና ባህርይ ምሳሌ ግን በኃጢአት አበላሸው ፣የተበላሸውን ለማደስ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ወልድ(ቃል) ሰው ሆነ፣ ሥጋ ለበሰ። በእርሱ ሞት በሦስቱ አካላትና(በሥላሴ) በሰው ልጆች መካከል ዕርቅ ተደረገ።
ዕርቁም ሦስት ትልልቅ ነገሮችን አስገኘ፦
1. ልጅነትን
2. ምስጋናን
3. ዘለዓለማዊነትን
1. ልጅነት:—አብን አባት ብሎ መጥራት፣ ለወልድ የባህርይ አባቱ ሲሆን ፣ወልድ የእኛን ሥጋ በመልበሱ ለእኛ የጸጋ አባታችን እንዲሆን አደረገ ፣ዮሐ1÷12፣20÷17
2. ምስጋና:—የነበረብን የጥል ግድግዳ ፈርሶ "ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ………) ብሎ ከመላእክት ጋር ማመስገን፣ ቃል ወልድ ሰው ስለሆነልን በኢመዋቲ ልሳን ማመስገን።
3. ዘለዓለማዊነት:—የማንሞት ፣የማንፈርስ የማንበሰብስ ሆነን መነሣት
እነዚህ ሁሉ ከሦስቱ አካላት ጋር በጸጋ ያገኘናቸው ሱታፌዎች ሲሆኑ "አዳም ኮነ ከመ አሐዱ እምኔነ" (አዳም ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ) ዘፍ 3÷22 ብሎ ራሱ ባለቤቱ የተናገረው በባህርይ ሳይሆን በጸጋ እንደተፈጸመልን ያጠይቃል፣ሃይማኖታችን ከአብ ጀምሮ (በመወለድ) በመንፈስ ቅዱስ (በዘለዓለማዊ ሕይወት) ይታተማል!!!
ይህ ምሥጢረ ሃይማኖት ይባላል፡፡፡
ሊቁ ይህን ሲያይ "በመንፈስ ቅዱስ ትፈጸማለች አለ!" ለዚህም ነው ሃይማኖት ሰማያዊ ዘለዓለማዊ ቋንቋ ነው ያልነው፣ ሁሉ ሲያልፍ ፣ ጠፈርና ምድር ድራሻቸው ሲጠፋ ሃይማኖት የሰውና የመላእክት የልጅነት፣የምስጋና የዘለዓለማዊ ሕይወት ቋንቋ ሆኖ ይቀጥላል ፣ ጌታም እንዲህ አለ:—"ሰማይና ምድር ያልፋሉ፣ ቃሌ ግን አያልፍም" ማቴ 24÷35
"ቃሌ" ያለው ሃይማኖት መሆኑን ልብ ይሏል፣ ለኒቆዲሞስ ያስተማረው ራሱ ነውና፣ ዮሐ 3÷1—12።
ይህን ቀጥተኛና ዘለዓለማዊ ሕይወት የምታስተምረን ይህች "ሐዋርያዊት፣ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን" ናት ፣ ዛሬ በዓለም ብዙ ነገሮች እየተሰሙ ነው፣ ነገር ግን እነዚህ ድርጅቶች እንጂ ሃይማኖት አይደሉም ፣ ሃይማኖት በህዝብ ቁጥር ልክ ሳይሆን በሰው ልክ ነው፣ ሰው ደግሞ አንድ ነው!! ሃይማኖትም አንድ ነው! ሃይማኖት ዘመንአመጣሽ አይደለም፣ ሥላሴ ዘመን አመጣሽ ስላልሆኑ! ምሥጢረ ሥላሴ በዘመን ስለማይለካ!
ትውልድ ሃይማኖቱን ሊከተለው ይገባል እንጂ ሃይማኖቱ ትውልድን አይከተለውም፣ እንዲያ ከሆነ ሰው የሥላሴ ተከታይ መሆኑ ቀርቶ ሥላሴ የሰው ተከታይ ሆኑ እንደማለት ይሆናል፣ ለዚህም ነው ሰው ሃይማኖቱን መለወጥ የሌለበት፣ ሃይማኖት ማንነታችን ስለሆነ! ሃይማኖት አንድ ጊዜ የተሰጠ መሆኑንንም ሐዋርያው ይሁዳ ሲመሰክር እንዲህ ብሏል
" ወዳጆች ሆይ፥ ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ" ይሁዳ 1 : 3
ሃይማኖት ምን ማለት እንደሆነ ስንረዳ ስናውቅ ፣ ማንነታችንና በውስጣችን እየተቀጣጠለ ፣እየተብላላ የሚኖር ተፈጥሯዊ ኃይል መሆኑን ስናውቅ ለእግዚአብሔር እናድራለን፣ ክርስተያናዊ ሥራም እንሰራለን ፣ መንግሥቱንና ጽድቁን እንወርሳለን። ሃይማኖት በቃል የሚጠና ብቻ ሳይሆን በተግባር እስከሞት ድረስ በሚከፈል ዋጋ የሚገለጥ በመሆኑ ብቻውን ጥቅም እንደሌለው ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክት ነግሮናል ፣ " እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው።"
የያዕቆብ መልእክት 2 : 17፡፡
(ተሻሽሎ በድጋሚ የተለጠፈ)
አምላካችን እግዚአብሔር በሃይማኖት ፀንተን ምግባር ትሩፋት ሠርተን የመንግሥቱ ወራሾች አንድንሆን ይርዳን!
የሞቱትን ወገኖቻችንን ነፍስ ይማር!!!
መዋዕለ ጾሙን በሰላም ያስፈጽመን
አሜን!!!
ነቅዐ-ጥበብ ከፍያለው ዘመካኒሳ ሚካኤል See less
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment