Monday, December 2, 2019

እነዚህን መልዕክቶች በማስተዋል ይመልከቷቸው
የኃጢአተኛውን ፡ ጥፋት ( Yehatiategnawn Tefat ) - ተስፋዬ ፡ ጋቢሶ
አዝ፦ የኃጢአተኛውን ፡ ጥፋት
እግዚአብሔር ፡ መቼ ፡ ይወዳል?

የተጣለ ፡ ሰው ፡ እንኳን ፡ ፈጽሞ ፡ እንዳይጠፋ
በምክሩ ፡ ያስባል ፣ በምክሩ ፡ ያስባል


ምሕረትና ፡ ዕውነት ፣ ፍቅርና ፡ ቸርነት ፡ የሞላው ፡ ጌታ

ኃጥዕ ፡ በንስሐ ፡ ይቀበል ፡ ይቅርታ

ማንም ፡ እንዳይጠፋ ፡ መድህን ፡ ሞቶልናል

ክርስቶስ ፡ ኢየሱስ ፡ ቤዛ ፡ ሆኖልናል


አዝ፦ የኃጢአተኛውን ፡ ጥፋት
እግዚአብሔር ፡ መቼ ፡ ይወዳል?

የተጣለ ፡ ሰው ፡ እንኳን ፡ ፈጽሞ ፡ እንዳይጠፋ
በምክሩ ፡ ያስባል ፣ በምክሩ ፡ ያስባል


ሰው ፡ ግን ፡ በውድቀቱ
ለምን ፡ ተስፋውን ፡ ይቆርጣል ፡ ቶሎ?

ለምን ፡ ይቀናዋል ፡ መውረድ ፡ አሽቆልቁሎ?

ጌታን ፡ እጠብቃለሁ ፣ ቢገድለኝም ፡ ብሎ

በዕምነት ፡ የሚቆም ፡ አይቀርም ፡ ጐስቁሎ


አዝ፦ የኃጢአተኛውን ፡ ጥፋት 
እግዚአብሔር ፡ መቼ ፡ ይወዳል?
የተጣለ ፡ ሰው ፡ እንኳን ፡ ፈጽሞ ፡ እንዳይጠፋ 
በምክሩ ፡ ያስባል ፣ በምክሩ ፡ ያስባል


የሚወደውን ፡ ልጅ ፡ እግዚአብሔር
ለጥቅሙ ፡ ይቀጣዋል

መክሮ ፡ ይገስጸዋል ፣ ያስተካክለዋል

በአባትነት ፡ ዓይኑ ፡ ይመለከተዋል

ሲፍገመገም ፡ ቢያየው ፣ ፍጥኖ ፡ ይደግፈዋል


አዝ፦ የኃጢአተኛውን ፡ ጥፋት
እግዚአብሔር ፡ መቼ ፡ ይወዳል?

የተጣለ ፡ ሰው ፡ እንኳን ፡ ፈጽሞ ፡ እንዳይጠፋ
በምክሩ ፡ ያስባል ፣ በምክሩ ፡ ያስባል
1ኛ ) እግዚአብሔር በደለኛውን ንጹሕ ነህ አይልም ኃጢአትን ይቀጣል ነገር ግን ይሄው እግዚአብሔር ተመልሶ በምሕረት ይረዳል ይቅርም ይላል
ለእነዚህ ዋና ዋና ሃሳቦች የተጻፈልንን የእግዚአብሔር ቃል አስረጂ አቀርባለሁ
እግዚአብሔር ትዕግስተኛ ኃይሉም ታላቅ ነው በደለኛውን ንጹሕ ነህ አይልም እግዚአብሔር በወጀብና በአውሎ ነፋስ ውስጥ መንገድ አለው ደመናም የእግሩ ትቢያ ነው ( ትንቢተ ናሆም 1 ፥ 3 )
እግዚአብሔር ለዚህ ሕዝብ እንዲህ ይላል መቅበዝበዝን ወደዋል እግራቸውንም አልከለከሉም ስለዚህ እግዚአብሔር በእነርሱ ደስ አይለውም በደላቸውንም አሁን ያስባል ኃጢአታቸውንም ይቀጣል ( ትንቢተ ኤርምያስ 14 ፥ 10 )
ኃጢአትን የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች፤ ልጅ የአባቱን ኃጢአት አይሸከምም፥ አባትም የልጁን ኃጢአት አይሸከምም፤ የጻድቁ ጽድቅ በራሱ ላይ ይሆናል፥ የኃጢአተኛውም ኃጢአት በራሱ ላይ ይሆናል ( ትንቢተ ሕዝቅኤል 18 ፥ 20 )
እንግዲህ፦ በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ አልኋችሁ፤ እኔ እንደሆንሁ ባታምኑ በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁና አላቸው ( የዮሐንስ ወንጌል 8 ፥ 24 )
2ኛ ) ይህን አውቀው ለተመለሱና ለሚመለሱ ብቻ ሳይሆን መመለስም ያለው ከእግዚአብሔር እርዳታ የተነሳ ስለሆነ ሊመለሱ የእግዚአብሔርን እርዳታ ለሚናፍቁ ሁሉ የእግዚአብሔር ምሕረት እንደገናም የምሕረት እርዳታውም ሆነ ይቅር ማለቱ አለ

እግዚአብሔር የረዳኝ ባይሆን ነፍሴ ለጥቂት ጊዜ በሲኦል ባደረች ነበር እግሮቼ ተሰናከሉ ባልሁ ጊዜ አቤቱ ምሕረትሕ ረዳኝ አቤቱ ለልቤ እንደ መከራዋ ብዛት ማጽናናሕ ነፍሴን ደስ አሰኛት ( መዝሙር 93 ( 94 ) 16 _ 19 )
ገፋኸኝ ለመውደቅም ተንገደገድኩ እግዚአብሔር ግን አገዘኝ
መዝሙር ( 118 )፥ 13
አቤቱ አምላኬ እየኝ ስማኝም ጠላቴ አሸነፍኩት እንዳይል የሚያስጨንቁኝም እኔ ብናወጥ ደስ እንዳይላቸው ለሞትም እንዳልተኛ ዓይኖቼን አብራ እኔ ግን በቸርነትሕ ታመንሁ ልቤም በመድኃኒትሕ ደስ ይለዋል የረዳኝን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ ለልዑል እግዚአብሔር ስምም እዘምራለሁ ( መዝሙር 12 ( 13 ) ፥ 3 _ 6 )
እኔ ግን በምሕረትሕ ብዛት ወደ ቤትሕ እገባለሁ አንተን በመፍራት ወደ ቅድስናሕ መቅደስ እሰግዳለሁ ( መዝሙር 5 ፥ 6 )
ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሳ ነው ርኅራኄው አያልቅምና ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው ታማኝነትሕ ብዙ ነው ( ሰቆቃወ ኤርምያስ 3 ፥ 22 እና 23 )
ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለጸጋ ስለሆነ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሳ በበደላችን ሙታን እንኩዋ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወትን ሰጠን በጸጋ ድናችኋልና በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለጠግነት ያሳይ ዘንድ ከእርሱ ጋር አስነሳን እያለ ይቀጥላል ( ኤፌሶን 2 ፥ 4 _ 10 )
3ኛ ) የምሕረት ባለጸግነትና ፍቅሩ ስላላለቀ እግዚአብሔር የኃጢአተኛውን ጥፋትም ሆነ የሟቹን ሞት አይወድምና የወደቀ ይነሳል የሳተ ይመለሳል
እግዚአብሔርስ ሞገሱን ረሳን፧ በቍጣውስ ምሕረቱን ዘጋውን፧ ( መዝሙር ( 77 ) ፥ 6 _ 11
ሁላችን እንሞታለን፥ በምድርም ላይ እንደ ፈሰሰና እንደማይመለስ ውኃ ነን፤ እግዚአብሔርም የነፍስን ጥፋት አይወዽም፥ ነገር ግን የተጣለ ሰው ፈጽሞ እንዳይጠፋ በምክሩ ያስባል
( 2ኛ ሳሙኤል 14 ፥ 14 )
የምዋቹን ሞት አልፈቅድምና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ስለዚህ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ ( ትንቢተ ሕዝቅኤል 18 ፥ 32 )
እንዲህም ትላቸዋለህ፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የወደቁ አይነሡምን ? የሳተስ አይመለስምን ? ( ትንቢተ ኤርምያስ 8 ፥ 4 - 6 )
ስለዚህ እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ 1ኛ ቆሮንቶስ 10 : 12
ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፥ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል
( 2ኛ ጴጥሮስ 3 ፥ 9 )
ተባረኩ
አባ ዮናስ

No comments:

Post a Comment