Thursday, December 12, 2019


እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደሆነ እወቁ 
እርሱ ሰራን እኛም አይደለንም 
እኛስ ሕዝቡ የመሠማርያውም በጎች ነን 

መዝሙር 99 ( 100 ) 3

የተወደዳችሁ ቅዱሳን ሰላም ለእናንተ ይሁን 

የምንባቡን ክፍል ስንመለከት እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደሆነ እወቁ እርሱ ሰራን እኛም አይደለንም ማለቱ ሰሪነቱን ፣ ፈጣሪነቱን ያመለክታል :: ከዚህ እውነት አንጻር ዛሬ ላይ ቆመን የእግዚአብሔርን ፈጣሪነትና ሰሪነት ስናስብ ከሰዎች አስተሳሰብና የምልልስም ሆነ የሕይወት ሥርዓት ብልሽት አንጻር  የእግዚአብሔር ፈጣሪነቱም ሆነ ሰሪነቱ ያልተከበረበት ደረጃ ላይ እንደደረስን እናስተውላለን :: መጽሐፍቅዱሳችንም ስለዚህ ጉዳይ እንዲህ በማለት ይገልጽልናል ::  የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና ፤ ስለዚህም እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙት አጡ ፤ ነገር ግን በአሳባቸው ከንቱ ሆኑ የማያስተውለውም ልባቸው ጨለመ ጥበበኞች ነን ሲሉ ደንቆሮ ሆኑ የማይጠፋውንም የእግዚአብሔር ክብር በሚጠፋ ሰውና በወፎች አራት እግር ባላቸውም በሚንቀሳቀሱትም መልክ መስለው ለወጡ ስለዚህ እርስ በርሳቸው ሥጋቸውን ሊያዋርዱ እግዚአብሔር በልባቸው ፍትወት ወደ ርኵስነት አሳልፎ ሰጣቸው ይህም የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት ስለ ለወጡ በፈጣሪም ፈንታ የተፈጠረውን ስላመለኩና ስላገለገሉ ነው ፤ እርሱም ለዘላለም የተባረከ ነው፤ አሜን ስለዚህ እግዚአብሔር ለሚያስነውር ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባውን ሥራ ለባሕርያቸው በማይገባው ለወጡ እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ወንዶችም በወንዶች ነውር አድርገው በስሕተታቸው የሚገባውን ብድራት በራሳቸው ተቀበሉ እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው ዓመፃ ሁሉ፥ ግፍ፥ መመኘት፥ ክፋት ሞላባቸው፤ ቅናትን፥ ነፍስ መግደልን፥ ክርክርን፥ ተንኰልን፥ ክፉ ጠባይን ተሞሉ፤ የሚያሾከሹኩ ሐሜተኞች፥ አምላክን የሚጠሉ፥ የሚያንገላቱ፥ ትዕቢተኞች፥ ትምክህተኞች፥ ክፋትን የሚፈላለጉ፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ የማያስተውሉ፥ ውል የሚያፈርሱ፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ምሕረት ያጡ ናቸው እንደነዚህ ለሚያደርጉት ሞት ይገባቸዋል የሚለውን የእግዚአብሔርን ሕግ እያወቁ እነዚህን ከሚያደርጉ ጋር ይስማማሉ እንጂ አድራጊዎች ብቻ አይደሉም ይለናል  በሮሜ 1 21 - 32 )የተጻፈውን እንመልከት:: 

ውድ ወገኖቼ ሆይ ይህ የተጻፈው ቃል እንዳለ ሆኖ በሰዎች ሕይወት ላይ ተግባራዊ እየሆነ መምጣቱ ሲገርመን ከዚህ የመገረምና የሃዘኔታ ሕይወት ሳንወጣና ሳናገግም  ደግሞ ይባስ ተብሎ  ሕዝቡና የመሠማርያውም በጎች ነን የተባልነው እኛ  በዚህ በሮሜ 1 21  - 32 ባለ ክፉ ሃሳብ ተጠልፈን  የእግዚአብሔርን ፈጣሪነቱንም ሆነ ሰሪነቱን በመዘንጋት የመሠማርያው በጎች ልንሆን እግዚአብሔርም ሊያሰማራን የተቸገረብን ፍየሎች መሆናችን በእጅጉ ያሳዝናል :: ዛሬ ላይ እኛስ ሕዝቡ የመሠማርያውም በጎች ነን የተባልን ቅዱሳን ከዚህ ይልቅ የዓመጻን መንገድ መርጠን ራሳችንን በራሳችን መንገድ ላይ ያሰማራን ብልጣብልጥ ፍየሎች ሆነናል :: በብሉይ ኪዳኑ የመሥዋዕት ሥርዓት ደንብ የነበሩትን ሁለት ፍየሎች ብንመለከት እነዚህ ሁለት ፍየሎች በማስተስረያ ስነ ሥርዓት ቀን ይቀርቡ ነበር :: ታድያ አንዱ ይታረድ ሁለተኛው ግን ይለቀቅ እንደነበረ መጽሐፍቅዱሳችን ይጠቁመናል :: ( ዘሌዋውያን 16 7 - 22 ) ታድያ ከእነዚህ ከሁለቱ ፍየሎች መሃል አንዱ ታርዶ ሌላኛው መለቀቁ ትልቁን  ትምህርት የሚሰጠን ነው :: ታድያ ለእነዚህ ለሁለት ፍየሎች የመታረድም ሆነ የመለቀቅ ፈቃድ የተገኘው ከአራጁም ሆነ ከለቃቂው በተገኘ ፈቃድ ነው እንጂ ከፍየሎቹ አለመሆኑን ልናስተውል ይገባል :: ይህንን ስል ታድያ ራሱን ያረደም ሆነ የለቀቀ ፍየል አለመኖሩን ልጠቁማችሁ  ነው :: ይህንን ሁኔታ እንግዲህ እንደብሉይ ኪዳኑ ሥርዓት አስተውለን ከተመለከትነው መሥዋዕት ሊሆን የሚታረደው በጉ ብቻ ሳይሆን ፍየሉም ነው እያልኩ ነው ፣ ስለዚህ አንደኛው  ይታረዳል  ሌላኛው ፍየል ደግሞ ይለቀቃል :: ይህንን እውነታ ዛሬ ላይ  ታድያ ወደ እኛ ዘመን ስናመጣው  ሁሉም ብልጣብልጥ ሆኖና በየራሱም ምክንያት ተሸፍኖ ራሱን የለቀቀ ፍየል እንጂ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሆኖ የሚታረድም ሆነ የሚለቀቅ ፍየል ግን አሁን በእኛ ዘመን አይገኝም ::  ለዚህም ነው ጴጥሮስ ይህንን ቃል የጠቀሰልን ቃሉም እንዲህ ይላል :: በጎ እያደረጋችሁ፥ የማያውቁትን ሞኞች ዝም ታሰኙ ዘንድ እንዲህ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነውና አርነት ወጥታችሁ እንደ እግዚአብሔር ባሪያዎች ሁኑ እንጂ አርነት ለክፋት መሸፈኛ እንዲሆን አታድርጉ ሁሉን አክብሩ፥ ወንድሞችን ውደዱ፥ እግዚአብሔርን ፍሩ፥ ንጉሥን አክብሩ ( 1ኛ ጴጥሮስ 2 15 - 17 ) :: ፍየሎች በባሕርያቸው ጠንካሮች ሆነው በድርቅ ሀገር ሊኖሩ ቢችሉም ፍየሎች አሁንም ክርስቶስን ያልተከተሉ ሰዎች ምሳሌ ናቸው (ማቴዎስ 25 33 ) ታድያ የዛሬውም ክርስቲያን እንደ እኔ ያለ አገልጋዩንም ልትሉት ትችላላችሁ ከአነጋገሩ ከአሰባበኩና ከሰላምታው ተነስታችሁ አሁን ላይ የእግዚአብሔርን ፈቃድ አውቆ ክርስቶስን የተከተለ የክርስቶስ በግና የእግዚአብሔር ባሪያ ነው ብትሉትም ጠጋ ብላችሁ ሕይወቱን ስትመረምሩ ግን አርነቱን ለክፋት መሸፈኛ እንዲሆን ያደረገ በቃሉ መሠረት ሁሉን  ከማክበር ይልቅ ማዋረድን ገንዘቡ ያደረገ ፣ ወንድሞችንም ከመውደድ ይልቅ መጥላትን እግዚአብሔርን ከመፍራትና  ንጉሥንም ከማክበር ይልቅ እግዚአብሔርን መዳፈርና ሹማምንትንም መዘርጠጥ ተግባሩ ያደረገ አለሌ ፍየል ነው :: እግዚአብሔር ሳይለቃቸው  ራሳቸውን ኤፍታ ሲሉ የለቀቁ ጻድቃን መሳይ ፍየሎች ደግሞ ከዓመጻ ብዛት የተነሳ ዛሬ ላይ ባለ ሕይወታቸው ሊሰሙንና ሊቀበሉን ባይወዱም መጨረሻቸው ግን የሚሆነው እንዲህ ነው ትንቢተ ኤርምያስ 2 2 20 - 37 የተጻፈውን ያንብቡ :: 

ውድ ወገኖቼ ሆይ ጌታ እግዚአብሔር ያስበን :: በመንገድ ላይ እንደተለቀቀ እንደ ፈጣል ግመል ሆነንም  ሰዎች ሳይደክሙ በወራታችን የሚያገኙንና እኛም በስንፍናችንም ሆነ በሌብነታችን ብዛት የምናፍር እንዳንሆን ቀን ሳለ ዛሬ እግዚአብሔር እግሮቻችንን ከሻካራው መንገድ ይመልስልን 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን ተባረኩ 

አባ ዮናስ ጌታነህ 

No comments:

Post a Comment