እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለመልአኩ ዜና ብስራት በሰጠችው ቃለ ተአምንሮ ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር ከጥንት ያሰበውና የፈቀደው ያድህነተ ዓለም ሥራ እንዲፈጸምና አማናዊ እንዲሆን አድርጋለች :: ይህም ወላዲተ አምላክ በነገረ ድኅነት ውስጥ ያላትን ታላቅ ሱታፌ በጉልህ ያሳያል :: ይህንን ምሥጢር በተመለከተ ኢትዮጵያዊው ሊቅ በድርሰቱ "" ዘበቃለ ጉሕሎቱ ለሰይጣን መልአክ ስሕተት ተሰፍሐ ግላ ጽልመት ውስተ ኩሉ ዓለም :ወበቃለ ብሥራቱ ለገብርኤል መልአክ ጽድቅ ተሰፍሐ ብርሀነ ሕይወት ውስተ ኩሉ ዓለም : የስሕተት አለቃ በሆነው በሰይጣን የክፋትና የጥፋት ቃል ምክንያት የጨለማ መጋረጃ በዓለም ሁሉ እንደተዘረጋ : የእውነት መልአክ በሆነው በቅዱስ ገብርኤል የምሥራች ቃል ደግሞ የሕይወት ብርሀን በዓለም ሁሉ ተዘረጋ በማለት መስክሯል :: ኢትዮጵያዊው የዜማ ሊቅ ቅዱስ ያሬድም እመቤታችን በነገረ ድህነት ውስጥ ያላትን ልዩ ሥፍራ ሲናገር "" በእንተ ተሠግዎቱ ለወልደ አምላክ እምኔኪ ቀሩባነ ኮነ እምድር ውስተ አርያም :ብኪ ወበከመ ወልድኪ "" ብሏል :: የዚህ ኃይለ ቃል ትርጉዋሜ ምሥጢርም ቃለ እግዚአብሔር ወልድ ከሥጋሽ ሥጋ :ከነፍሥሽ ነፍስን ነሥቶ ካንቺ ሰው በመሆኑ ከምድር ወደ ሰማይ :ከሞት ወደ ሕይወት : ከመርገም ወደ በረከት : ከኃሳር ወደ ክብር : ከሲኦል ወደ ገነት የተሸጋገርንብሽ ማለት ነው :: ከላይ የተጠቀሰውን በቃዲምት ሔዋንና በዳግሚተ ሔዋን መካከል ያለውን ምሥጢራዊ ንጽጽር አስመልክቶ
'' ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ ""በመባል የሚታወቀው ሊቁ ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ሲገልጽ "" ለእመ ኃሠሥላ ለሔዋን ትረክባ በህየ እንዘ ትትፌሣሕ በወለታ ዘእምጽአት ፈውሰ ለቁስሊሀ : ለእመ ኃሠሦኮ ለአዳም ረክቦ በህየ እንዘ ይትፌሣሕ ወይገብር በዓለ ምስለ ዳግማዊ አዳም "" በማለት በንጽጽሩ ውስጥ ያለውን ጥልቅና ረቂቅ ምሥጢረ ድህነት አስተምሯል :: እንደ ሊቁ አገላለጽ ዳግሚት ሔዋን የተባለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፍሬ ሕይወት ወመድኃኒት የሆነው ጌታ የተገኘባት አማናዊት ዕጸ ሕይወት በመሆኗ የዕጸ በለስን ፍሬ በልታ ሞትን ላመጣችብን ለቀዳሚቷ ሔዋን ካሣ ናት :: ምክንያቱም ከዳግሚት ሔዋን ከድንግል ማርያም የተወለደው የማኅጸኗ ፍሬ ጌታችን መድኃኒታችን አምላካችን ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሚያርቅ :በረከተ ሥጋ :በረከተ ነፍስን የሚያድል ሕይወተ ሥጋን ሕይወተ ነፍስን የሚሰጥ : ቀዳሴ ሥጋ ወነፍስ ወመንፈስ የሆነ ቡሩክ አምላክ ነውና ::
No comments:
Post a Comment