Friday, January 1, 2021

 

ትምህርተ ሃይማኖት (ክፍል ሦስት)
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ )፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ከኹሉም በፊት አንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ማወቅ ያለበት
አንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ከኹሉም በፊት ስለ ነገረ ቤተ ክርስቲያን፣ ስለ ቅዱስ ትውፊት፣ ስለ ቅዱሳት መጻሕፍት የአተረጓጐም ስልት፣ ስለ ዶግማ እና ስለ ቀኖና በጥቂቱም ቢኾን ማወቅ አለበት፡፡ አስቀድሞ ከእነዚኽ መሠረታውያን ትምህርቶች ጋር የተዋወቀ ክርስቲያን በትምህርተ ሃይማኖት (ዶግማ) ውስጥ ለሚኖረው ትምህርት መሠረትን ይይዛል፡፡ የእነዚኽን ጽንሰ ሐሳብ ያልተረዳ እንደኾነ ግን ጭራሽኑ የክርስትናን ጽንሰ ሐሳብም ሊስተው ይችላል፡፡ የብዙዎች ከቤተ ክርስቲያን መጥፋትም በአንድም ይኹን በሌላ መልኩ የእነዚኽ ኦርቶዶክሳዊ ጽንሰ ሐሳቦች የዕውቀት ማነስ ነው፡፡ ኹሉንም አንድ በአንድ የምንመለከታቸው ሲኾን ለዛሬ ከነገረ ቤተ ክርስቲያን እንዠምራለን፡፡
ሀ) ኦርቶዶክሳዊ የነገረ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ (Orthodox Teaching of Ecclessiology)
ትርጕም
ነገረ ቤተ ክርስቲያን ስንል ስለ ቤተ ክርስቲያን ያለው ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ምን እንደኾነ የምንማርበት የትምህርት ዘርፍ ነው፡፡ ምንም እንኳን ትምህርቱ እጅግ ጥልቅና ራሱን የቻለ ሰፊ መጽሐፍ የሚወጣው ቢኾንም በዚኽ ክፍል ግን በነገረ ሃይማኖት ትምህርታችን ውስጥ አስቀድመን ልናውቀው ስለሚገባው ነገር ብቻ ለማንሣት እንሞክራለን፡፡
ቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃል ሦስት ዓይነት ሰዋስዋዊና ዘይቤአዊ ትርጕም አለው /አባ ጐርጐርዮስ (ሊቀ ጳጳስ)፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ፣ ገጽ 12-17/፡፡
• የመዠመሪያው የተወሰነ ቦታን ያመለክታል፡፡ ይኸውም የክርስቲያኖች ቤት፣ መኖሪያ ማለት ነው /1ኛ ቆሮ.11፡18/፡፡ “ቤተ ክርስቲያን እንሒድ” /መዝ.121፡1/ ሲባልም ይኽን ፍቺ የያዘ ነው፡፡ በመጻሕፍትም ቤተ ክርስቲያን ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔር ቤት ተብላለች /ዘፍ.18፡27፣ መዝ.5፡7፣ መዝ.26፡4፣ መዝ.83፡4፣ መዝ.92፡5፣ ሉቃ.2፡49፣ 1ኛ ጢሞ.3፡15፣ ዕብ.10፡21/፡፡
• ኹለተኛው ደግሞ ክርስቲያኖች ራሳቸው ቤተ ክርስቲያን ይባላሉ /1ኛ ቆሮ.3፡16፣ 1ኛ ቆሮ.6፡19/፡፡ ይኸውም በመንፈሳዊና በምሥጢራዊ ልደት ከክርስቶስ የተወለዱ፥ ርሱ አድሮባቸው የሚኖሩ፥ ከቅዱሱ ቅባት /1ኛ ዮሐ.2፡20/ እና ከሥጋ ወደሙ የተካፈሉ ምእመናንን ለማመልከት ነው፡፡
• ሦስተኛው ትርጕሙ ደግሞ የክርስቲያኖችን ኅብረት (ጉባኤን) የሚያመለክት ነው /1ኛ ጴጥ.5፡13/፡፡ እኛም በዚኹ ክፍል ትኵረት የምናደርገው በዚኹ በሦስተኛው ትርጓሜ ላይ ነው፡፡
እኛ በግእዝ ቤተ ክርስቲያን የምንለው ጽርዓውያን (ግሪካውያን) “ኤክሊሲያ” ይሉታል፡፡ ትርጓሜውም “ለአንድነትና ለአንድ ልዩ ዓላማ የተጠሩ” ማለት ነው፡፡ ይኸውም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስኅብረት የጠራችኁ እግዚአብሔር የታመነ ነው” ብሎ ከገለጸው ጋር የተስማማ ነው፤ የቤተ ክርስቲያን ዓላማ ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር አንድነትና ልዩ (ሰማያዊ) ዓላማ በሃይማኖት መጥራት ነውና /1ኛ ቆሮ.1፡9/፡፡

No comments:

Post a Comment