ለስዕል ይሰገዳልን?

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

41፥37 ሌሊትና ቀንም ፀሐይና ጨረቃም ከምልክቶቹ ናቸው፡፡ *ለፀሐይና ለጨረቃ “አትስገዱ”፡፡ ለእዚያም ለፈጠራቸው ለአላህ “ስገዱ” ፡፡ እርሱን ብቻ “የምታመልኩ” እንደ ኾናችሁ ”ለሌላ አትስገዱ”*፡፡ وَمِنْ آيَاتِهِ اللَّيْلُ وَالنَّهَارُ وَالشَّمْسُ وَالْقَمَرُ ۚ لَا تَسْجُدُوا لِلشَّمْسِ وَلَا لِلْقَمَرِ وَاسْجُدُوا لِلَّهِ الَّذِي خَلَقَهُنَّ إِن كُنتُمْ إِيَّاهُ تَعْبُدُون

በግሪክ “ኢኮን” εἰκών በዕብራይስጥ “ኤሊል” אֱלִיל ማለት “ስዕል”image” ማለት ሲሆን በሰሌዳ ላይ በቀለም፣ በጠመኔ፣ በእርሳስ አለዚያም በሌላ ነገር ተስርቶ በዓይን በማየት የሚገነዘቡት የአንድ ማንነት ወይም ምንነት ምስል ነው። አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ላይ ሥዕልን እንዲህ ይገልጹታል፦
ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፤ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግሥ ወመዝገበ ቃላት 673
*”ስዕል ማለት በቁም መልክ፣ የመልክ ጥላ፣ ንድፍ፣ አምሳል፣ ንድፍ በውኃ፣ በመጽሔት፣ በጥልፍ፣ በስፌት ወይም በቀለም በወረቀት ገዝፎ ተጽፎ ከደብር፣ ከእብን፣ ከእጽ፣ ከማዕድን ታንጦ፣ ተቀርጦ፣ ተሸልሞ፣ አጊጦ የሚታይ የሚዳሰስ ነገር ነው*፡፡”

ያህዌህ ሙሴን በተራራው ሰማያዊ ኑባሬዎችን በመገለጥ እያሳየው እነዚያን ኑባሬዎች በምስል አድርጎ እንዲሰራ አዞት ነበር፦
ዘጸአት 25፥40 *በተራራ ላይ እንዳሳየሁህ ምሳሌ እንድትሠራ ተጠንቀቅ።
ዘጸአት 26፥30 *ማደሪያውንም በተራራ እንዳሳየሁህ ምሳሌ አቁም*።
ዕብራውያን 8፥5 እነርሱም *ሙሴ ድንኳኒቱን ሊሠራ ሳለ እንደ ተረዳ፥ ለሰማያዊ ነገር ምሳሌና ጥላ የሚሆነውን ያገለግላሉ። በተራራው እንደ ተገለጠልህ ምሳሌ ሁሉን ታደርግ ዘንድ ተጠንቀቅ ብሎት ነበርና*።
የሐዋርያት ሥራ 7፥44 *እንዳየው ምስል አድርጎ ይሠራት ዘንድ ሙሴን ተናግሮ እንዳዘዘው*፥ የምስክር ድንኳን ከአባቶቻችን ዘንድ በምድረ በዳ ነበረች።

“እንዳየው ምስል አድርጎ ይሠራት ዘንድ ሙሴን ተናግሮ እንዳዘዘው” የሚለው ሃይለ-ቃል ይመሰርበት፤ ይህም ምስል የመላእክትን ምስል ይጨምራል፤ ለምሳሌ የኪሩቤል ምስል እንዲሰራ ታዞ ነበር፦
ዘጸአት 25፥19 ከስርየት መክደኛውም ጋር *አንዱን ኪሩብ በአንድ ወገን፥ ሁለተኛውንም ኪሩብ በሌላው ወገን አድርገህ በአንድ ላይ ትሠራዋለህ*።

ኪሩብ በነጠላ ሲሆን በብዜት ደግሞ ኪሩቤል ነው። ያህዌህ ሕዝቅኤልን፦ “የኢየሩሳሌምንም ከተማ ስዕል ሳልባት” ብሎ አዞት ነበር፦
ሕዝቅኤል 4፥1 አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ጡብን ወስደህ በፊትህ አኑራት *የኢየሩሳሌምንም ከተማ ስዕል ሳልባት ክበባት*፥

ይህ እንዲህ በእንዲህ እንዳለ ነቢያት ይህንን ሥነ-ጥበብ ሰውን ለማስተማር ይጠቀሙበት ነበር እንጂ አንድም ቀን ሰግደውለት አያውቁም፥ ስገዱለት የሚል መመሪያም አልተቀበሉም አላስተላለፉም። ከዚያ በተቃራኒው የሙሴ አምላክ ለሙሴ፦ “የተቀረጸም ምስል ወይም ሐውልት አታቁሙ፤ ትሰግዱለትም ዘንድ በምድራችሁ ላይ የተቀረጸ ድንጋይ አታኑሩ፣ የማናቸውንም ምሳሌ፥ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ፣ አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውምም” ብሎ አዞልታ፤ እንደውም መዝሙረኛው፦ “ለተቀረጸ ምስል የሚሰግዱ ሁሉ ይፈሩ” ይላል፦
ዘሌዋውያን 26፥1 እኔ ያህዌህ አምላካችሁ ነኝና ለእናንተ *”ጣዖት አታድርጉ፥ የተቀረጸም ምስል ወይም ሐውልት አታቁሙ”፤ ትሰግዱለትም ዘንድ በምድራችሁ ላይ የተቀረጸ ድንጋይ አታኑሩ*።
ዘጸአት 20፥4 በላይ በሰማይ ካለው፥ በታችም በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር *”የማናቸውንም ምሳሌ፥ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ፤ አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውምም”*፤
መዝሙር 97፥7 *”ለተቀረጸ ምስል የሚሰግዱ ሁሉ፥ በጣዖቶቻቸውም የሚመኩ ይፈሩ*”፤ መላእክቱ ሁሉ ስገዱለት።

የሰው እጅ ሥራን የተቀረጸ ምስልን የሚያደርግ፥ በስውርም የሚያቆመው ሰው በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላና የተረገመ ነው። ነቢያትም የተቀረጸውን ምስል ሠራተኛ እንደሚሰራው፣ የተቀረጸውን ምስል የሚሠሩ ከንቱ እንደኾኑ እና ለእጃቸውም ሥራ ስለ ሰገዱ ፍርድ በእነርሱ ላይ እንደለ ተናግረዋል፦
ዘዳግም 27፥15 *በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ የሠራተኛ እጅ ሥራን የተቀረጸ ወይም ቀልጦ የተሠራ ምስልን የሚያደርግ፥ በስውርም የሚያቆመው ሰው ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ መልሰው አሜን ይላሉ*።
ኢሳይያስ 40፥19 *የተቀረጸውንስ ምስል ሠራተኛ ሠርቶታል*፥ አንጥረኛም በወርቅ ለብጦታል፥ የብሩንም ሰንሰለት አፍስሶለታል።
ኢሳይያስ 44፥9 *የተቀረጸውን ምስል የሚሠሩ ሁሉ ከንቱዎች ናቸው*፥
ኤርምያስ 1፥16 ስለ ክፋታቸውም ሁሉ፥ እኔን ስለ ተው ለሌሎችም አማልክት ስላጠኑ *ለእጃቸውም ሥራ ስለ ሰገዱ፥ ፍርዴን በእነርሱ ላይ እናገራለሁ*።

ሰው ለሠራው የእጅ ሥራ እንዴት ይሰገዳል? በኦርቶዶክስ፣ በካቶሊክ እና በአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለስዕል የጸጋ ስግደት ይሰገዳል፤ ልብ አድርግ የጸጋ ስግደት ስገዱ የሚል ትእዛዝ የለም። በተቃራኒው ለተቀረጸ ምስል “አትስገድላቸው” የሚል ትእዛዝ ቢኖር እንጂ። ነገር ግን ይህ ግዑዝ ነገር በዐበይት ክርስቲያኖች ይሰገድለታል፥ ምስጋና ይቀርበለታል፤ ይህ በተግባር ሲሆን በጽሑፍ ደግሞ ታምረ-ማርያም የዘወትር መቅድም ላይ እና መልክአ ስዕል ላይ እንዲህ የሚል መመሪያ አለ፦
የዘወትር መቅድም ቁጥር 35-36 ገጽ 7
ግዕዙ፦
*ወቅድመ ስዕላ ስግዱ! ዘኢሰገደ ላቲ ይደምስስ እምቅዋሙ ወኢይትዐወቅ ዝግረ ስሙ። ወይበሉ መላእክተ ሰማይ ኲሎሙ አሜን*።

ትርጉም፦
*በስዕሏ ፊት ስገዱ! ለሥዕሏ ያልሰገደ ግን ከቆመበት ቦታ ይጥፋ! ስም አጠራሩ አይታወቅ። በሰማይ ያሉ መላእክትም ይደረግ ይሁን ይበሉ*።

መልክአ ሥዕል ዘበዓለ ሃምሳ አርኬ 20
“ወእሰግድ ካዕበ ለድንግልናኪ ክልኤ፤ *”ወእሰግድ ሠልሰ ለስዕልኪ ቅድመ ጉባዔ፤ ዘኢሰገድ ለስዕልኪ አስሪጾ ምማኤ በሥጋሁ ወበነፍሱ ኢይርከብ ትንሳኤ*”።

ትርጉም፦
:በሁለት በኩል ድንግል ነሽና እሰግድልሻለው፤ *ለስዕልሽም በጉባኤ ፊት ሥስት ጊዜ እሰግዳለሁ፤ ለስዕልሽ ከመስገድ ወደ ኋላ ያለ በነፍሱም በስጋውም ትንሳኤ አያግኝ”*።

ነቢያት፦ “ለተቀረጸ ምስል የሚሰግዱ ሁሉ ይፈሩ” ሲሉ፥ ፈጣሪ “ለእጃቸውም ሥራ ስለ ሰገዱ፥ ፍርዴን በእነርሱ ላይ እናገራለሁ” ሲል ይህ በትውፊት የተቀመጡት አዋልድ መጽሐፍት ደግሞ፦ “በስዕሏ ፊት ስገዱ! ለስዕሏ ያልሰገደ ግን ከቆመበት ቦታ ይጥፋ” “ለስዕልሽም በጉባኤ ፊት ሥስት ጊዜ እሰግዳለሁ፤ ለስዕልሽ ከመስገድ ወደ ኋላ ያለ በነፍሱም በስጋውም ትንሳኤ አያግኝ” የሚል እርግማን ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው? ለምስል መስገድ እኮ 666 ለሆነው ለክርስቶስ ተቃዋሚ መንገድ የሚጠርግ ነው፦
ራእይ 13፥15 *”የአውሬው ምስል ሊናገር እንኳ ለአውሬውም ምስል የማይሰግዱለትን ሁሉ ሊያስገድላቸው፥ ለአውሬው ምስል ትንፋሽ እንዲሰጠው ተሰጠው”*።

አውሬው ወደፊት የሚመጣው የዓለማችን መንግሥት ነው፤ ለእዚያ መንግሥት ምስል 666 የተባለው ሐሰተኛው ነቢይና መሢሕ እንዲሰግዱ ያደርጋል፤ ታስታውሱ እንደሆነ በሮማውያን ጊዜ የቄሳር ምስል እና ጽሕፈት በሳንቲም ላይ ይሳል ነበር፦
ማርቆስ 12፥16 እነርሱም አመጡለት። *ይህች “ምስል” εἰκών እና ጽሕፈቲቱስ የማን ናት? አላቸው፤ እነርሱም፦ የቄሣር ናት አሉት*።

በተመሳይይ ለእዚህ መንግሥት ምስል ስለው እንዲሰገለት ያደርጋሉ። ለምስሉም የሰገዱትን ያሳተ ሐሰተኛው ነቢይና መሢሕ ሆነ ለምስሉም የሚሰግዱ በጀሃነም ስቃይ ቀንና ሌሊት ዕረፍት የላቸውም፦
ራእይ 19፥20 አውሬውም ተያዘ በእርሱም ፊት ተአምራትን እያደረገ የአውሬውን ምልክት የተቀበሉትን *ለምስሉም የሰገዱትን ያሳተ ሐሰተኛው ነቢይ ከእርሱ ጋር ተያዘ፤ ሁለቱም በሕይወት ሳሉ በዲን ወደሚቃጠል ወደ እሳት ባሕር ተጣሉ*።
ራእይ 16፥2 ፊተኛውም ሄዶ ጽዋውን በምድር ውስጥ አፈሰሰ፤ *የአውሬውም ምልክት ባለባቸው ለምስሉም በሚሰግዱ ሰዎች ክፉኛ የሚነዘንዝ ቍስል ሆነባቸው*።
ራእይ 14፥9-11 ሦስተኛም መልአክ ተከተላቸው፥ በታላቅ ድምፅ እንዲህ እያለ፦ *ለአውሬውና ለምስሉ የሚሰግድ* በግምባሩም ወይም በእጁ ምልክቱን የሚቀበል ማንም ቢኖር፥ እርሱ ደግሞ በቍጣው ጽዋ ሳይቀላቅል ከተዘጋጀው ከእግዚአብሔር ቍጣ ወይን ጠጅ ይጠጣል፥ በቅዱሳንም መላእክትና በበጉ ፊት በእሳትና በዲን ይሳቀያል። የሥቃያቸውም ጢስ ለዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ይወጣል፥ *ለአውሬውና ለምስሉም የሚሰግዱ የስሙንም ምልክት የሚቀበል ሁሉ ቀንና ሌሊት ዕረፍት የላቸውም*።

ይህንን አስፈሪ ወንጀል እያየ ወደ ክርስትና የሚገባ ሰው ቂል ካልሆነ ወይም በጥቅማ ጥቅም አሊያም በተቃራኒ ጾታ ፍቅር መነደፍ ካልሆነ በስተቀር አይሞክረውም። ይህንን ፍርድ እያወቀ ወደ ኢሥላም የማይመጣ በእሳት የሚጫወት ነው፦
41፥37 ሌሊትና ቀንም ፀሐይና ጨረቃም ከምልክቶቹ ናቸው፡፡ *ለፀሐይና ለጨረቃ “አትስገዱ”፡፡ ለእዚያም ለፈጠራቸው ለአላህ “ስገዱ” ፡፡ እርሱን ብቻ “የምታመልኩ” እንደ ኾናችሁ ”ለሌላ አትስገዱ”*፡፡ وَمِنْ آيَاتِهِ اللَّيْلُ وَالنَّهَارُ وَالشَّمْسُ وَالْقَمَرُ ۚ لَا تَسْجُدُوا لِلشَّمْسِ وَلَا لِلْقَمَرِ وَاسْجُدُوا لِلَّهِ الَّذِي خَلَقَهُنَّ إِن كُنتُمْ إِيَّاهُ تَعْبُدُون

” እርሱን ብቻ የምታመልኩ እንደ ኾናችሁ ለሌላ አትስገዱ” የሚለው ሃይለ-ቃል ይሰመርበት። በኢሥላም ፈጣሪ ከሆነው ከአንዱ አምላክ ከአላህ ውጪ የሚሰገድለት ማንነት ሆነ ምንነት የለም። ስዕል የሰው እጅ ሥራ ነው፤ ለዚህ ግዑዝ ነገር የምትሰግዱ ካላችሁ ጊዜው ሳይረፍድ ወደ አላህ በንስሃ ተመለሱ። ከአላህ በቀር የምትጠሯቸው ሊረዷችሁ አይችሉም፤ እራሳቸውንም አይረዱምና፦
7፥197 *እነዚያም ከእርሱ በቀር የምትጠሯቸው ሊረዷችሁ አይችሉም፤ እራሳቸውንም አይረዱም*። وَٱلَّذِينَ تَدْعُونَ مِن دُونِهِۦ لَا يَسْتَطِيعُونَ نَصْرَكُمْ وَلَآ أَنفُسَهُمْ يَنصُرُونَ

✍ከወንድም ወሒድ ዑመር
https://t.me/Wahidcom

ወሰላሙ አለይኩም