ከስማዝያ እስከ አዛዝኤል የወደቁ መልአክት ወይስ የሴት ልጆች ደቂቀ ሴት?
መጽሐፈ ሄኖክ ምዕራፍ 2 1_4 (2000 እትም)
« የሰው ልጆች ከበዙ በኋላ እንዲህ ሆነ
በእነዚያ ወራት መልከ መልካሞችና ደመ
ግቡዎች ሴቶች ልጆች ተወለዱላቸው የሰማይ ልጆች መላእክትም እነርሱን አይተው ወደዷቸው እርስ በርሳቸውም ኑ ለእኛ ከሰው ልጆች ሴቶችን እንምረጥ ለእኛም ልጆችን እንውለድ አሉ አለቃቸው ስማዝያ እኔስ ይህ ሥራ ይሠራ ዘንድ ምናልባት አትወድዱ እንደ ሆነ እፈራለሁ የዚህችም ታላቅ ኀጢኣት ፍዳ ተቀባይ እኔ ብቻ እሆናለሁ አላቸው »
መጽሐፈ ሄኖክ 19፥10 (1980 እትም)
«የነዚያም የአጋንንት ስማቸው እነሆ እንዲህ ነው የደቂቀ ሴትም ስማቸው ይህ ነው »
«የእነዚያም መላእክት ስማቸው እነሆ ስማቸው ይህ ነው» (መጽሐፈ ሄኖክ 19፣10 2000 እትም) አዲሱ የ2000 እትም ላይ ደቂቀ ሴት የሚለው ወጥቶ አጋንንት ሳይሆን መልአክ ተብለው ተጠርተዋል የስም ዝርዝራቸው ከዚህ በታች ያለውን ይመስላል፥
አለቃቸው ሰማዝያ ነው፦
2 አርስጢኪፋ 3 አርሚን 4 ኮከብኤል
5 ጡርኤል 6 ሩምያል 7 ዳንኤል
8 ምቃኤል 9 በራቃኤል 10 አዛዝኤል
11 አርማሮስ 12 በጠርያል 13 በስላኤል
14 አናንያል 15 ጡርያል 16 ሲምሳፖኤል
17 ይታርኤል 18 ቱማኤል 19 ጥራኤል
20 ራሙኤል 21 አዛዝኤል
(መጽሐፈ ሄኖክ 19፥11-14)
እነዚህን አካላት መጽሐፍ ቅዱስ በ66 ቱ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ተጠርተዋል፥ በኦርቶዶክ አማኞች ተቀባይነት ባለው በ81ዱ እና የብሉይ ኪዳን ተጨማሪ በሚባሉት እንደ መጽሐፈ ሄኖክ መቃቢያን እና ኩፋሌ ላይ በ1980 እትም ደቂቀ ሴት(የሴት ልጆች) እና አጋንንት በአዲሱ የ2000 እትም ላይ ደግሞ መልአክ እያለ በተለያየ ስም ይጠራቸዋል።
ክርስቲያን ወገኖቻችንም እነዚህ አካላት፦ "ደቂቀ ሴት ናቸው፥ ከንጽህናቸውና ከቅድስናቸው የተነሣ ለፈጣሪ ታዛዥ በመሆናቸው የእግዚአብሔር ልጆች /መልአኮች/ ተባሉ እንጂ ትክክለኛ መልአክ ስለሆኑ አይደለም" የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ እስኪ እውነቱን እንፈትሸው፦
1ኛ ፦ እዚህ በላይ ስማቸው የተጠቀሱት አካላት የሴት ልጆች ናቸው ከተባለ በሴት የትውልድ ዝርዝር ውስጥ የተወሰኑትን ልናገኛቸው ይገባ ነበር፦ ቅሉ ግን የአንዳቸውንም ስም እንኳን ማግኘት አንችልም። የሴት የትውልድ ሐረግ ላይ የአንዳቸውም ሰም አለመገኘቱ የእርሱ ልጆች እና የልጅ ልጆች ላለመሆናቸው አንደኛው ማሳያ ነው።
2ኛ፦ "ለሰው ልጆች ያስተማሩት ትምህርት
እነዚህ አካላት በደብረ ቅዱስ በቅድስና እግዚአብሔርን እያመለኩ የነበሩ የሴት ልጆች( ደቂቀ ሴት) ናቸው" ከተባለ መጥተው ለሰው ልጆች አስተማሩ ከተባለው ነገር ጋር ይጣረሳል፥ ምን አስተማሩ?
መጽሐፈ ሄኖክ 2፥11 « ሟርትን ምታት ማሳየትን ኣስተማሩዋቸው ሥር መማስን ቅጠል መበጠስንም አመለከቷቸው። »
መጽሐፈ ሄኖክ 2፥18 « ኣዛዝዔልም ለሰዎች ሾተልና ሰይፍ መሥራትን ጋሻ መሰጐድንም ጥሩር መሥራትንም አስተማራቸው። »
መጽሐፈ ሄኖክ 2፥21« አሚዛራክ ጋኔን መሳብን ምታት ማሳየትን ሥር መማስን ቅጠል መበጠስንም ሁሉ አስተማረ አርማሮስም ጋኔን መሳብን አስተማረ። »
መጽሐፈ ሄኖክ 2፥22-23 « ኮከብኤልም ምልክት ማሳየትን ኣስተማረ ፣ ጥሞኤልም ኮከብ መቁጠርን አስተማረ።»
መጽሐፈ ሄኖክ 19፥27-28 « አምስተኛውም ስሙ ከዕድያዕ ይበላል፥ የነፍሳትና የአጋንንትን ያመጡትን ክፉ መማታትን ሁሉ ለሰው ልጆች ያሳየ እሱ ነው ከማኅፀን ወጥቶ ይወድቅ ዘንድ ፅንስ ማስወረድን ነፍስ መግደልንም ያስተማረ እሱ ነው »
እነዚህ አካላት "በቅድስና እግዚአብሔርን እያመለኩ ይኖሩ የነበሩ የሴት ልጆች ናቸው" ከተባለ ካስተማሩት ድርጊት ጋር እንዴት ይሄዳል? እግዚአብሔርን በቅድስና እያመለከ የሚኖር ሰው መግደልን፣ መተትና ሟርትን፣ ፅንስ ማስወረድን፣ ጋኔን መሳብን ከየት ያውቀዋል ነው? በእናንተ እምነት ቅድስና ማለት እነዚህ እና መሰል ክፉ ስራዎች ናቸው?
3ኛ፦ ሔዋንን ያሳሳታት ጋድርኤል
እዚህ ላይ ልትገነዘቡት የሚገባው ትልቁ ነጥብ ይህ "ጋድርኤል የተባለው አካል ሔዋንን ያሳሳታት እሱ ነው" ተብሎ ተገልጿል መቸ ነው ያሳሳታት ? እንደሚታወቀው እነዚህ አካላት ከሰው ልጆች ጋር ተጋቡ በተባለበት ሰዓት አይደለም። ሔዋን ሴትም በሕይወት አልነበረም ታዲያ ሔዋን ባልነበረችበት ዘመን ጋድርኤል እሷን እንዴት አሳሳተ? በተጨማሪም አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋሰው ገጽ 242 ላይ ጋድርኤል ማለት ፦ የጋኔን ስም ሔዋንን ያሳሳተ ሰይጣን በማለት መጽሐፈ ሄኖክ 19፥19 መረጃ አድርገው አስቀምጠውታል።
4ኛ ፦ የወለዷቸው ልጆች ርዝመት
መጽሐፈ ሄኖክ 2፣3 « ወደነሱም ይገቡ ዘንድ ጀመሩ፣ ከነሱም ጋራ አንድ ሆኑ /ደርሱባቸው/ ሟርትን ምታት ማሳየትን አስተማሩዋቸው ሥር መማስን ቅጠል መበጠስንም አመለከቷቸው። እነሱም ፀንሰው ረጃጅሞች አርበኞች ልጆችን ወለዱ ቁመታቸውም ሦስት ሦስት ሺህ ክንድ ነው። »
ነገሩ አስቂኝና ለማመን የሚከብድ ቢሆንም የእነዚህ ልጆች ቁመት ሦስት ሺህ ክንድ ነው፥ ይህ ማለት አንድ ሺህ አምስት መቶ ሜትር (1,5 ኪሎ ሜትር )ያህል ይረዝማሉ ማለት ነው። በቀላሉ ለማነጻጸር ያህል የእነዚህ ልጆች ቁመት ዛሬ ላይ በዓለማችን በርዝመቱ አንደኛ ከሚባለው ዱባይ ከሚገኘው ቡርጅ ኸሊፍ ሕንጻ ጋር ሲወዳደር የተወለዱት ልጆች ቁመት ሕጻውን በ2 እጥፍ ይበልጡታል እንደማለት ነው። ታዲያ ይህን ታሪክ እውነት ነው እንኳን ብንቀበል ሰው ከሰው ጋር ተጋብቶ ይህንን አይነት ከሰው የተለየ አካል ይወልዳል?
እነዚህንና መሰል ምክኒያቶችን ይዘን ከላይ የተጠቀሱትን አካላት ማንንነት ስንፈትሽ የሴት ልጆች (ደቂቀ ሴት) እንዳልሆኑ እንረዳለን ማለት ነው።

No comments:
Post a Comment