አክሱም ላይ ያለው ታቦት ከግብጽ እንጂ ከኢየሩሳሌም አልመጣም ።
በአገራችን በ13ኛው ክፍለ ዘመን በሥልጣን ጥመኞች ከተመሠረተው ራሱን፦ « ሰለሞናዊ » ብሎ ከሚጠራው ሥረወ መንግሥት ጋር አብረው የተፈጠሩ አያሌ ተረቶች አሉ፥ ከእነሱም ውስጥ አንደኛው፦ "የሙሴ ጽላት በሰለሞን ጊዜ ወደ አገራችን በልጁ በቀዳማዊ ምኒልክ «ተሰርቆ» መጣ" የሚለው ምናባዊ ተረት ነው።
ተሰርቆ ከመጣው ጽላት ላይ አስርቱ ትዕዛዛት ተቀምጠዋል፥ ከትዕዛዛቱ አንዱ « አትስረቅ » ይላል። አትስረቅ የሚለውን ትዕዛዝ ሰርቀው በማምጣት ታሪክ ሰርተዋል ማለት ነው? 
በሥልጣን ጥማት ዓይናቸው ታውሮ መጽሐፍ ቅዱስን እንኳን ሽምጥጥ አድርገው በመካድ የለም፦ "ጽላቱ እኛ ጋር ነው" የሚል ተረት ፈጥረዋል፥ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደሚታወቀው የቃል ኪዳኑ ታቦት ሰለሞን ከሞተ በኃላ እዛው እስራኤል ውስጥ ነበር። በኃላም የባቢሎን ምርኮ ጊዜ በምረኮ እንደተወሰደና እንደጠፋ ተመዝግቧል።
አክሱም ጽዮን ላይ ታቦት መኖሩ እውነት ነው ግን ይህ ታቦት የመጣው ከግብጽ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ እንጅ ሰለሞን በነበረበት ጊዜ ከኢየሩሳሌም አይደለም። ይኽን አስመልክቶ አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ ባዘጋጁት፦ «አዲስ መዝገበ ቃላት » ላይ ያስቀመጡት እንዲህ ብለው ነው፦
"ጽዮን ፤« በአብርሃ ዐምባ በአኽሱም ቤተ ክርስቲያን ያለች የእመቤታችን ታቦት ኀዳር 21 ቀን የምትነግሥ ከሣቴ ብርሃን ሰላማ ከሚካኤል ታቦት ጋራ ከቅዱስ አትናቴዎስ ተቀብሎ ያመጣት የአትናቴዎስ መሆኗንም በ4ኛው ዮሐንስ ጊዜ ኹለት የአርመን መነኮሣት ያነሱት ፎቶ ግራፏ ( ሥዕሏ) ይመሰክራል። ክብረ ነገሥት ግን በቀዳማዊ ምኒልክ ዘመን ከኢየሩሳሌም በሌዋዊያን እጅ ወደ ኢትዮጵያ የመጣች ጽላተ ሙሴ ነች ይላል » ( ዐዲስ መዝገበ ቃላት ደስታ ተክለ ወልድ ገጽ 1017 )
እነዚህ ሁለቱ ታቦቶች ከግብጽ ወደ አገራችን የገቡ የመጀመሪያ ስለመሆናቸው ደግሞ፦
ታቦት ፤ « ከግብጽ መጥተው በአኽሱም የነበሩት መዠመሪያዎቹ ታቦቶችም ታቦተ ማርያምና ታቦተ ሚካኤል ናቸው »(ዐዲስ መዝገበ ቃላት ደስታ ተክለ ወልድ ገጽ 1250 )

No comments:
Post a Comment