Tuesday, June 18, 2024
ከአባ እስጢፋኖስ በኋላ የተነሱ ተሃድሶአውያን
ይህ የነ አባ እስጢፋኖስ እንቅሥቃሴ በጊዜው በነበረው የፖለቲካ የበላይነት ተዳፍኖ ቢቆይም ውስጥ ውስጡን ግን ሲሄድ እና ቀስ ብሎ ሲጓዝ የኖረ እንቅሥቃሴ ነው። ይህን ውስጣዊ እንቅሥቃሴ በርካታ ሊቃውንት በሥዉር ሲሳተፉበት ኖረዋል። ለምሳሌ ከነዚህ ሊቃውንት ውስጥ ጥቂቶች ከመጻሕፍቶቻቸው መረዳት እንደሚቻለው አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፤ አለቃ ታዬ፤ አለቃ ብላቴን ጌታ ሕሩይ፤ ፤ አለቃ ገብሩ ደስታ፤ ዘመንፈስ፤ የሚባሉ ሊቃውንት ሲሆኑ በደንብ ወደ አደባባይ ካወጡት እና ከቤተ ክርስቲያን ከተገለሉት የቅርብ ሊቃውንት ውስጥ አለቃ መሠረት ስብሐት ለአብ እና ጓደኞቻቸው ይገኙባቸዋል። የአለቃ መሠረት ስብሐት ለአብ ጓደኞች አሁንም በሕይወት ስለአሉ ስማቸውን መጽሐፍ አልፈለግሁም። እነርሱም ስማቸው እንዲወጣ አይፈልጉም። ዛሬም በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ በተለያዩ ሥራዎች ተመድበው ይገኛሉ። ከላይ ስማቸውን የጠቅስኋቸው ሰዎች የአባ እስጢፋኖስ ሐሳብ ነበራቸው። ይህን ለማለት ያስቻለኝ አሁን ያሉት ቤተ ክርስቲያን መታደስ አለባት የሚሉት ወገኖች ከሚያራምዱት አላማ ጋር መጻሕፍቶቻቸውን በማስታያየት እና የሕይወት ታሪካቸውን በማገናዘብ ነው።
የተሐድሶዎች ዓላማ ምንድን ነው?
ተሐድሶዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መሻሻል አለባት ይላሉ። ራእያቸውም ቤተ ክርስቲያኒቱ በሐዋርያት እምነት ላይ የተመሠረተች በመሆኗ፤ የሐዋርያትን ትምህርት መከተል አለባት። አሁን የሚታዩት የሕዝብ ልማዶች እንደ ሃይማኖት ሆነው የሚታዩት ከዘርዓ ያዕቆብ ዘመን ጀምረው በኃይል እና በፖለቲካ የበላይነት የተጫኑብን እንጂ እውነተኛው እና ጥንታዊው የኦርቶዶክስ እምነት አይደለም ባይ ናቸው። እውነተኛውን ኦርቶዶክሳዊ ትውፊትንም ሆነ እምነትን የሸፈነ ልማድ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አለ። ይህን ቀስ በቀስ ሕዝብን በማስተማር መሰረቱን ሳያፈርሱ ውሸት የሆነውን ሁሉ እናስወግዳለን የሚል ራእይ አላቸው።
ተሐድሶ እንዲደረግ የሚፈልጉትም፦
1ኛ በአምልኮው ላይ 2ኛ በመጻሕፍቱ ላይ 3ኛ በአስተዳደሩ ላይ ተሐድሶ እንዲደረግ ይፈልጋሉ። ለዚህም መጻሕፍቶቻቸውን ማንበብ ይቻላል በርካታ መጻሕፍት አሏቸው። በገድላት፣ በድርሳነ ሚካኤል እና በድርሳነ ገብርኤል በድርሳነ ኡራኤልም ላይ በጠቅላላ በድርሳናቱ እና በገድላቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ ትችታቸውን ጽፈዋል ወደ ፊት እናቀርበዋለን።
በአስተዳደር ላይ የሚያነሱት ጥያቄ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር ተመሳሳይ ነው።ልዩነቱ ማኅበረ ቅዱሳን አስተዳደሩ በራሱ ሰዎች እንዲያዝ የሚፈልግ ሲሆን ተሐድሶዎች ግን ለእውነት በቆሙ ሰዎች መያዝ አለበት በሚለው ነው።አስተዳደሩ መንፈሳዊ ካልሆኑ ሰዎች ተላቆ በተማሩ እና ፈሪሃ እግዚአብሔር ባላቸው ሰዎች ይመራ ባይ ናቸው። በአስተዳደሩ የሚፈጸሙ የዘረኝነት እና የሙስና አሠራርን አጥብቀው የሚቃወሙ ሲሆን በየቤተ ክርስቲያኑ በበዓል ቀን መንፈሳዊ ያልሆነ አሠራር እየተስፋፋ ነው። ይህም የንግድ ሥራ እንጂ የእምነት ሥራ አይደለም በማለት አጥብቀው ይቃወማሉ። ጠንቋዮች በቤተ ክርስቲያኒቱ መታቀፍ የለባቸውም። ጠንቋይ የሆኑ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ባዕድ አምልኮን በማስፋፋት ትልቁን ሚና እየተጫወቱ ስለሚገኙ ይወገዱልን ባይ ናቸው። በዚህ እረገድ ማህበረ ቅዱሳንም ጠንካራ አቋም አለው። የቀረውን የእንቅሥቃሴያቸውን ታሪክ በሚቀጥለው አቀርባለሁ። ከኔ የቀረውን አንባቢ ቢያስተካክለው ደስ ይለኛል።
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment