Tuesday, June 11, 2024
የመጽሀፍ ቅኝት፡ የነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ሥራዎች
የመጽሀፍ ቅኝት፡ የነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ሥራዎች
Rukya Hassen Shibeshi, #OPEN_TO_WORK
Rukya Hassen Shibeshi
Associate Professor at Kotebe University of Education
July 29, 2020
በዶ/ር ሩቅያ ሀሰን
ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ
የስነልሳንና ስነተግባቦት ተባባሪ ፕሮፌሰር
የነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝን ሁለት መጽሀፎች በአንድ ጥራዝ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ በ2003 ዓ.ም. አሳትሞታል፡፡ የነባር ምርጥ መጻህፍት ሕትመት በሚል ርእስ እያሳተማቸው ካለው መጽሀፎች ውስጥ ይህ ድንቅ ስራ በመካከቱ ፕሬሱ ሊመሰገን ይገባል፡፡ በዚህ መጽሀፍ በአንድ ጥራዝ የወጡት የነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ ስራዎች “አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ”ና “መንግስትና የህዝብ አስተዳደር” የተሰኙ ናቸው፡፡ ስራዎቹ እንዲታተሙ ሀሳብ ያቀረቡት የወቅቱ የፕሬሱ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ እንደሆኑ የየነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ የልጅ ልጅ የሆኑት ወ/ሮ ዓይናለም አሸብር ገብረ ሕይወት ገልጸዋል፡፡
ለመጽሀፉ መግቢያ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ እንዲሁም ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ ጽፈዋል፡፡ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ በመጽሀፉ ጀርባ ላይም እንደታተመው ስለደራሲው ሁለት አስገራሚ ነገሮችን ሲጠቅሱ አንደኛው ገብረ ሕይወት ይህን የመሰለ እስካሁን ድረስ የሚያስተጋባ ጥልቅ የኢኮኖሚና ፖለቲካ ጉዳዮችን በሰላሳዎቹ እድሜ መጻፍ መቻላቸውና ሁለተኛው የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ባልሆነው በአማርኛ ውብና አጥንት የሚሰረስር ስራ ጽፈው ማለፋቸው ነው፡፡ የሞቱት በ33 ወይም በ37 አመት እድሜያቸው በ1911 ከአውሮፓ በመጣው የንፋስ (ግሪፕ) የወረርሽኝ በሽታ እንደሆነ በመጽሀፉ ተገልጧል፡፡ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ በሁለተኛው መጽሀፍ ላይ ሰፋ ያለ አድናቆት ያስቀመጡ ሲሆን የብዙ ኢኮኖሚክስ ሀሳቦች ባለቤት እንደነበሩና ከሳቸው ከ50ና 60 አመት በኋላ የመጡ ምእራባውያን ኢኮኖሚስቶች የሳቸውን ሀሳብ በባለቤትነት ወስደው እንደሚታወቁበት ነገር ግን አሁንም የነጋድራስ ሞዴል እያሉ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ የሚጠሯቸው አዳዲስ የኢኮኖሚክስ ሀሳቦች እንዳሏቸው በከፍተኛ አድናቆት ጽፈዋል፡፡
“አጤ ምኒሊክና ኢትዮጵያ”
ነጋድራስ ለመንግስትና ለህዝባቸው በርካታ ምክሮችን በመጀመሪያው “አጤ ምኒሊክና ኢትዮጵያ” በተሰኘው መጽሀፍ ላይ ያሰፈሩ ሲሆን በመጀመሪያ ምክሮቹ ለአጤ ምንሊክ የታቀዱ የነበሩ ቢሆንም በኋላ ግን ምክሮቹ ለልጅ እያሱ እንዲሆኑ በሚል ጽፈዋቸዋል፡፡ መጽሀፉ አጭር ሲሆን ትልልቅና ቁልፍ ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡ ነጋድራስ ካነሷቸው ቁልፍ ምክሮች ውስጥ ጥቂቶቹን እናነሳለን፡፡
ታላቁ ምሁር ነጋድራስ ገብረህይወት ከመቶ አመት በፊት በጻፉት በዚህ አስደናቂ መጽሀፋቸው ለአንድ ህዝብ ስርአት ወይም ሲስተም እንደሚያስፈልግ ሲገልጹ “የሀይል ምንጭ ሥርአት ነው እንጅ የሰራዊት ብዛት አይደለም” ብለዋል፡፡ ላለመሰልጠናችንና ላለማደጋችንም በአስተሳሰብ ባለመብሰላችን መሆኑን ሲገልጹ ደግሞ እንዳሉት “እኛ ኢትዮጵያውያን ካለመስማማታችን የተነሳ ሌሎች ህዝቦች በአእምሮና በጥበብ እየበረቱ ሲሄዱ እኛ ወደ ኋላ ቀረን” ነበር (ነጋድራስ ገ/ሕይወት 2003፣ 19)፡፡
በሚገርም ሁኔታ ነጋድራስ ገብረህይወት ከመቶ አመት በፊት የጠቀሱት ጉዳይ ነገር ግን እኛን አሁን በደንብ የሚገልጸን የሚከተለው ገለጻቸው ነው፡፡
በመላው አለም ላይ ሰላም ሲሰፋ አእምሮም ስትበራ እኛ በጨለማ እንኖራለን፡፡ እርስ በርሳችን መጠራጠራችንንም አልተውንም፡፡ ህዝቦቹም ሁሉ እርስ በርሳቸው በፍቅር ተቃቅፈው ስለልማታቸው ባንድነት ሆነው ሲደክሙ እኛ ግን ዘርና ወንድማማች መሆናችንን ገና አልተገለጸልንም፡፡ እርስ በርሳችን መፋጀትም እስከ ዛሬ ድረስ ጀግንነት ይመስለናል፡፡ ስለዚህ እግዚያብሄር ለብርታት የሚሆነውን ስጦታ ሁሉ ሰጥቶን ሳለ ባለቤቶቹ ሰነፍነ፡፡ ለሌሎቹም ነገስታት እንደ ሰነፎች ይቆጥሩናል፣ ይንቁናልም (ነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ 2003፣ 19-20)፡፡
ነጋድራስ ገብረህይወት የድህነታችንን ምክንያት ሲገልጹ የሚከተለውን አስቀምጠዋል፡፡
ህዝቡም ሀብታም የሆነ መንግስት ብርቱ ነው፡፡ ህዝቡ የደኸየ እንደሆነ ግን ደካማ፡፡ እኛ ግን ስርአት የለንም፡፡ ስለዚህ ሰነፍን፡፡ በመሬታችን ውስጥ የተሸሸገውም ሀብት ፈላጊ አጣ፤ ስለዚህም ደኸየነ… ምነው የኢትዮጵያ ህዝብ ከእንቅልፍህ መቸ ትነሳለህ? (ነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ 2003፣ 22)፡፡
ጽሁፍ ለማህበረሰብ እድገት መሰረታዊ መሆኑን ሲገልጹ እንዳሉት “የተጻፈ ስርአት የሌለው መንግስት ብዙ እድሜ የለውም” (ነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ 2003፣ 25)፡፡
ከሁሉም በላይ ለዚህ ዘመን ነዋሪ እጅት በጣም የሚያስገርመው የነጋድራስ ገብረህይወት ሀሳቦች ውስጥ የሚጠቀሰው ስለሃይማኖት የጻፉት ነው፡፡ የሀይማኖት ነጻነት መኖር እንዳለበትና ሀይማኖት ከልብ የሆነ መሆኑንና ዳኛውም ፈጣሪ መሆኑን የገለጹበት መንገድ አስገራሚ ነው፡፡
ደግሞም ባገራችን አንድ የድንቁርና ነገር አለ፡፡ ሃይማኖቱ ተዋህዶ ያልሆነ ሁሉ እንደ ርኩስ ይቆጠራል፡፡ ይህም እጅግ ያስቃል፡፡ አእምሮ የሌለው ህዝብ ሁሉ የእግዚያብሄርን ቃል ሳያውቅ የእግዚያብሄር ጠበቃ ሊሆን ይወዳል፡፡ … ሀይማኖት የልብ ነው፡፡ ስለዚህ ሰማያዊው ንጉስ አንጅ የዚህ አለም ንጉስ አይቆጣጠረውም (ነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ 2003፣ 28)፡፡
ስለርእዮተ አለም ሲመክሩ ነጋድራስ ይህንን ብለው ነበር “ኢትዮጵያችን የኤሮጳን አእምሮ የተቀበለች እንደሆነ የሚደፍራት ጠላት የለም፡፡ ያልተቀበለች እንደሆነ ግን ትፈርሳለች፤ ወደ ባርነትም ትገባለች” (ነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ 2003፣ 28)፡፡
በስተመጨረሻ የመጀመሪያውን መጽሀፍ ያገባደዱት “መንግስታችንም እንድትቀና የሚከተሉት አሥር ነገሮች በቶሎ ቢፈጸሙ ማለፊያ ነበር” (ነጋድራስ ገብረህይወት፣ 2003፡ 23-27) ያሉትን በማቅረብ ነበር፡፡
1. ለመንግስት የሚሆን ገንዘብና ለንጉሱ የሚሆነውን ገንዘብ በሥርአት ይለይ፡፡ ሹሞቹም በደሞዝ ይደሩ፡፡ ካገር የሚወጣውም ግብር ለመንግስት ይግባ፡፡
2. ሕዝቡ ለመንግስት የሚከፍለው ግብር እንደየሀብቱ መጠን ቁርጥ ሁኖ ይታወቅለት፡፡ የሕዝቡም ቁጥር በመዝገብ ይግባ፡፡ እንዲሁም በየአመቱ የሚወለደውና የሚሞተውም የሚጋባውና የሚፋታውም በመዝገብ ይታወቅ፡፡
3. ሕዝቡም የሚከፍለው ግብር በብር እንጅ በእህል በማርም በፍሪዳም አይሁን፡፡ የመንግስት ስራ ሁሉም በባላገር አይስራ፤ በባለ ደሞዝ እንጅ፡፡
4. ያማርኛ ቋንቋ ገና ሰዋሰው አልተበጀለትም፡፡ ስለዚህ መንግስታችን ከያገሩ ሰዋሰው የሚያዉቁትን ሊቃውንት ሰብስቦ ያማርኛን ቋንቋ ሰዋሰው ቢያስወጣ ደግ ነው፡፡… ያገራችን ሰው ፊደልን ለመማ ቢተጋ አገራችን ቶሎ በቀናች፡፡ ፊደልንም መማር እጅግ ቀላል ነገር ነው፡፡
5. ፍትሐ ነገሥታችን (ህጋችን) ከዛሬው ያደባባይ ሥርአት ጋር አይስማማም፡፡ ስለዚህ መንግስት የሥርአት አዋቆችን ሰብስቦ ከኤሮጳ ሥርአት ጋር የተስማማ ፍትሐ ነገስት ያውጣ፡፡
6. ያገራችን ሰራዊት ስርአት የለውም፡፡ ስለዚህ የኤሮጳን መኳንንት አምጥተው ሰልፍን ቢማር ማለፊያ ነበር፡፡ እንዲሁም የኤሮጳን መምህራን አምጥተው ባዲስ አበባ ላይ የጦር ትምህርት ቤት ይበጅ፡፡
7. የዛሬው የመንግስታችን ብር የተበላሸ ነው፡፡ ሥርአት ውል የለውም፡፡ ስለዚህ መንግስት ለመላው ኢትዮጵያ የሚሆን የገንዘብ ሥርአት በቶሎ ያላወጣ እንደሆነ ንግድ ሊለማ አይችልም፡፡
8. ላገራችን ነጋዴ ሥርአት እስኪወጣለት ድረስ መንግስታችን አይቀናም፡፡ በሩና (ኬላው) ቀራጩ ብዙ ነው፡፡ በአንድ መንግስት ውስጥ አንድ ነጋዴ በየበሩ መቀረጥ የለበትም፡፡
9. ህዝቡ ባንድ መንግስት ውስጥ መሆኑን አጥብቆ እንዲታወቀው አገሩን የሚዞሩ ተቆጣጣሪዎች ይሾሙበት፡፡
10. የሀይማኖት አርነት ይታወጅ፡፡ የሃይማኖት አርነት ቢታወጅ ሃይማኖት ይታወቃል እንጅ አያጠፋም፡፡ ሃይማኖት የልብ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ሰማያዊው ንጉስ እንጅ የዚህ ዓለም ንጉስ አይቆጣጠረውም፡፡
“መንግስትና የህዝብ አስተዳደር”
ሁለተኛው መጽሀፍ “መንግስትና የህዝብ አስተዳደር” ሰፋ ያለ ሲሆን ደራሲው በርካታ ቁልፍ ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡ ይህ መጽሀፍ ኢኮኖሚክስ፣ ገንዘብ፣ ንግድና የመሳሰሉ ሱዳዮችን ይዳስሳል፡፡ ለሁሉም ነገር ቁልፉ ትምህርት እንደሆነ ሲገልጹ ይህንን ብለዋል “መንግስት ሀይል ለማግኘት የፈለገ እንደሆነ ህዝቡ እንዲበለጽግና እንዲማር መጣር ያስፈልገዋል” (ነጋድራስ ገብረህይወት 2003፣ 36)፡፡
ስለዋጋ ሲናገሩ “ዋጋ ማለት የስራ መለኪያ ማለት ነው” (ነጋድራስ ገብረህይወት 2003፣ 68)፡፡ የኑሮውድነትና ጫናን ለመቀነስ እውቀት ቁልፍ እንደሆነ ነጋድራስ እኛን የመከሩን ከመቶ አመት በፊት እንደዚህ ብለው ነው “እውቀት ሲበዛ ለኑሮ የሚያስፈልገውን ማናቸውንም ነገር ለማግኘት መሰናክሉ ያንሳልና የማናቸውም ዋጋ ሁሉ ዝቅ ይላል” (ነጋድራስ ገብረህይወት 2003፣ 71)፡፡ ትምህርት ለአንድ ህዝብ የጀርባ አጥንት መሆኑን ሲገልጹ “ህዝቡ እንዳይጎዳ የሚፈልግ መንግስት ሁሉ አውራ ጥረቱ ትምህርት እንዲበዛ ነው” (ነጋድራስ ገብረህይወት 2003፣ 75)፡፡
ነጻነት በእውቀትና በትምህርት የሚገኝ መሆኑን ሲገልጹ “ሰው በአለም ላይ ጌታ የሆነው ግን በእውቀቱ ብቻ ነው፡፡… እውቀት የሌለው ህዝብ ሁሉ ለብቻው መንግስት ቢኖረውም ባይኖረውም እውቀት ላቸው ህዝቦች ይገዙታል” (ነጋድራስ ገብረህይወት 2003፣ 75)፡፡ እውቀት ለሰው ልጅ መበልጸጊያና ማደጊያ መሰረታዊ መሳሪያ መሆኑን ሲያሰምሩ “እውቀት አለምን እንዲገዛ የማይነቃነቅ ዘላለማዊ ደንብ ነው” ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ደራሲው የሰው ልጅ ሲፈጠር ጌታና ሎሌ እንዲሆን እንዳልነበረ አጽንኦት ሰጥተው አብራርተዋል፡፡ ፈጣሪ የሰውን ልጅ በምድር ሲያስቀምጥ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ አሟልቶለት እንደሆነም በሚመስጥ አገላለጽ ገልጸውታል “ለሰው የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ምድር በሆዷ ይዛለች፡፡… ማናቸውንም ነገር ሲፈልግ አንቀሳቅሶ ማጋጠም ብቻ ነው ያለበት፡፡ ማንቀሳቀስና ማጋጠም የሚሆነው በስራ ነው፡፡ ስለዚህ የሰው እውቀቱና ገንዘቡ ስራ ብቻ ነው” ይሉናል (ነጋድራስ ገብረህይወት 2003፣ 80)፡፡
በእውቀት፣ በስራና በጥረት ላይ የተመሰረተ ለውጥን የሚያቀነቅኑት አስገራሚው ነጋድራስ ገብረህይወት “ሰውም ምድርን የሚገዛበት ምክንያት በእውቀት ነው እንጅ በጉልበት አይደለም” ያሉን ከ100 አመት መሆኑ ነገር ግን እና እስካሁን አዲስ ነገር እየሆነብን መሆኑ ይገርማል፡፡ እሳቸው ግን አበክረው “እውቀት የሌለው ህዝብ ሀብታም ሊሆን አይችልም” ብለውናል (ነጋድራስ ገብረህይወት 2003፣ 83)፡፡
የሰው ልጅ ምድርን ለመግዛት እንጅ በምድር ለመገዛትና የምድር ሎሌ ለመሆን እንዳልተፈጠረ ያስረዳሉ፡፡ ነገር ግን ደሀ ከሆንን ሌላ አማራጭ አይኖረንም፡፡ ይህንንም በአሳማኝ ሁኔታ ሲያቀርቡት እንደዚህ በማለት ነው “ድሀ የሆነ ህዝብ የምድር ሎሌ ነው፡፡ በረሀብና በበሽታ በሞት ስታንገላታው ትኖራለች፡፡ ሀብታም ህዝብ ግን የምድር ጌታ ነውና ምድር ሎሌ ሆኖ ታገለግለዋለች” (ነጋድራስ ገብረህይወት 2003፣ 84)፡፡
ሌላው አስገራሚው የገብረሂወት ገለጻ ስለሀብት የሰጡት ነው፡፡ “ሀብት ማለት የተከማቸ ስራ ማለት ነው፡፡… እውቀት የሌለው ህዝብ ግን ሥራው አይከማችለትም፡፡ የፊት የፊቱ ወዲያው ያልቃል፡፡ ከድካሙም ፍሬ የሚያገኘው ጥቅም ጥቂት ነው፡፡ ስለዚህ እውቀት የሌለው ህዝብ ድሀና የሰው ሎሌ ነው” (ነጋድራስ ገብረህይወት 2003፣ 94)፡፡
ከውጭ ስለሚመጡና ስለምንገዛቸው ቁሶች ሲገልጹ “እውቀት ያነሳቸው ህዝቦች እውቀታቸው ከፍ ካለ ህዝቦች ላይ እቃ ሲገዙ እየተበደሩ ነው፡፡ የሚበደሩትም ብድር እኩሌታው ከጉልበታቸው እኩሌታው ከምድራቸው ነው” ይሉናል፡፡ ነጻነት ስላለው ህዝብ የሚከተለውን ማብራሪያ በመግለጽ ስለሀገራችን ነጻ መሆን ይጠይቃሉ
እስቲ አሁን እኛ የኢትዮጵያ ህዝብ አርነት አለን ነው? አርነት ያለው ህዝብ ማለት እውነተኛ ትርጉሙ ለብቻው መንግስት ያለው ህዝብ ማለት ብቻ አይደለም፤ ራሱን የቻለ ህዝብ ማለት ነው እንጅ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ እስከ ዛር ድረስ ገና ራሱን አልቻለም፡፡ እስቲ የለበስነውን እንይ፤ ከወዴት የተሰራና ማን ያመጣው ነው? የቤታችንስ እቃ ራሱ ከወዴት የመጣ ነው? የምንለብሰውስ ልብስ የምንጠጣውስ የምንበላበት ምግባችንን የምናበስልበት እቃና መስሪያ ሁሉ ፈጽሞ ከውጭ አገር የመጣ አይደለምን?” (ነጋድራስ ገብረህይወት 2003፣ 102)፡፡
የሀገር ሀብት የሚያንሰው ከሰሪው ይልቅ በላተኛው ሲበዛ መሆኑን ገልጸው ለሀገር ብልጽግና ሲባል እውቀት ብቻ ሳይሆን ሀብትም እንደሚያስፈልግ አበክረው እንደሚከተለው ይመክራሉ “የዚህ አለም ህዝቦች የለውጥ መሳሪያዎቻቸው ብርና ወርቅ ብቻ ስለሆኑ ብርና ወርቅ ያነሰበት ህዝብ ከፍ ወዳለው የእውቀት ደረጃ ደርሶ ሀብታም ሊሆን አይችልም” (ነጋድራስ ገብረህይወት 2003፣ 131)፡፡ በተጨማሪም መሰረታዊ ፍላጎቱን ያላሟላ ህዝብ የሀገር ፍቅር እንደማይኖረው በማሳሰብ የህዝብን ፍላጎት ማሟላት ለሀገር ደህንነት ቁልፍ ሚና እንዳለው በዚህ መልኩ ይነግሩናል “የሚበላውና የሚለብሰውንም ያጣ ድሀ የተወለደበትን አገር የሚወድበትን ምክንያት ያጣልና ያገሩ መንግስት ቢበረታ ወይም ቢጠፋ ግድ የለውም፤ ስለዚህ መንግስት የሚጠቁም ያገሩ ሀብት በጥቂቶች ሰዎች እጅ ቢሰበሰብ አይደለም፡፡ ያገሩን ሀብት በመላው ህዝቡ ሊከፋፈል ነው አንጅ” (ነጋድራስ ገብረህይወት 2003፣ 142)፡፡
ስርአት ወይም ሲስተም ከህዝብ ፍላጎት መመንጨት እንዳለበት ሲያብራሩ እንዳሉት “ስርአት የሚመች ይሆናል ተብሎ በብልሆች ሰዎች ልብ ውስጥ ተፈጥሮ አይጻፍም፤ ከህዝብ ልብ ቀዳል እንጅ፡፡ ንጉስ ወይም ሹም በኋለኞች ትውልዶች የሚመሰገንም በልቡ ፈልስፎ ደንብ ሲያወጣ አይደለም፡፡ የህዝቡን አሳብ ተርጉሞ በትርጉሙ ሲሄድ ነው እንጅ” (ነጋድራስ ገብረህይወት 2003፣ 147)፡፡
የህዝብና መንግስት መሰረት ትምህርት ቤት መሆኑን ያሰመሩበት ነጋድራስ ገብረህይወት “ትምህርት የሌለበት አገር አዲስ ደንብ ቢያወጣ ከሚጠቅመው የሚጎዳው ይበልጣል” ብለዋል (ነጋድራስ ገብረህይወት 2003፣ 148)፡፡
ስራን በመስራት ሀብት ለማካበት በምንጥርበት ወቅት መተማመን ቁልፍ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ብር የለውጥ መሳሪያ እንጅ ሌላ ፋይዳ ያለው ነገር እንዳልሆነ አስገንዝበዋል፡፡ የሰው ልጅም መልካምና መጥፎ ባህሪ እንዳለው ሲገልጹልን “የሰው ባህሪው ሁለት ነው፡፡ አንዱ መለኮታዊ፤ ሁለተኛው ግን እንስሳዊ ይባላል፡፡ ቀስቃሽ ካላገኘ ግን ሰው መልአካዊ ባህሪውን አይከተልም፡፡ ወደ እንስሳዊ ባህሪው ያደላል፡፡ ለሰው አውራ ቀስቃሽ ግን ባላንጣ ነው” (ነጋድራስ ገብረህይወት 2003፣ 164)፡፡
አንድ መንግስት አማካሪ እንደሚያስፈልገው የሚያመለክት አንድ ተጨባጭ ምክር በባንክ ዙሪያ የሚከተለው ተገልጧል
ዛሬ በኢትዮጵያ የቆመው ባንክ ኦፍ አቢሲን ከቆመበት ቀን ዠምሮ እስከ ሀምሳ አመት ድረስ በኢትዮጵያ ሌላ ባንክ እንዳይቆም ውል ተቀብሏል፡፡ ከዚህ ቀደም እንደተረዳነው ግን ማናቸውም ነገር የጥቂቶች ሰዎች እጅ ገብቶ ሞኖፖል ሲሆን ለህዝብም ለመንግስትም ጉዳት ው፡፡ ለአጼ ምኒሊክ አንድ ሰው መጥቶ ባገርዎ ከኔ በቀር ሌላ ሰው እንዳያርስ ወይም በቅሎ ገዝቶ እያከራየ እንዳይነግድ ወይም እኔን ሳይጠይቅ በየቤቱ ማንም ወጥ እየሰራ እንዳይበላ ፈቃድ ይስጡኝ ብሎ ለምኗቸው ቢሆን የሚያናግራቸው ቃል ምንም ቢያምር የሰጣቸው ተስፋ ምን ትልቅቢሆን ያለጥርጥር ይቆጡት ነበር (ነጋድራስ ገብረህይወት 2003፣ 163)፡፡
መንግስትና የህዝብ አስተዳደርን በተመለከተ ሀሳባቸውን በሚከተሉት በአስር ነጥቦች አጠቃለው አስቀምጠዋል (ነጋድራስ ገብረህይወት 2003፡ 124-126)፡፡
1. ሰው የተፈጠረ የምድር ጌታ ለመሆን ነበር፡፡ ነገር ግን በመዠመሪያ ጥቂት እራሱን ስለ ሆነ የሚበቃ መሳሪያ የለውምና የምድር ተገዥ ሆነ፡፡
2. በኋላ ግን እውቀት ስላገኘ ተባዛ ተባበረም
3. በዝቶ ከተባበረም ዘንድ ሥራውን ተከፋፍሎ የሰራውን ሥራ እንደየስራው መጠን መለዋወጥ ዠመረ፣ ዋጋ ማለት የስራ መለኪያ ነው እንዳልነው ሁሉ፡፡
4. ሀብት ማለት የአለም ጌትነት መለኪያ ነው፡፡ ማንቀሳቀስና ማጋጠም የሚሆነው በስራ ብቻ ነውና ሀብት ማለት የተከማቸ ስራ ማለት ነው፡፡
5. ማንኛውም የተሰራ ስራ ከኋላ የሚከተለውን ስራ ያቀላል፡፡ ማንኛውንም ሀብት የበለጠ ሀብት ይከተለዋል፡፡
6. የህዝብ ሀብት የሚሰፋው ህዝቡ የሚያስፈልገውን ሁሉ ለመስራት ስራውን በብዙ ተካፍሎ የተለዋወጠ እንደሆነ ነው፡፡
7. የድካማቸውን ፍሬ የሚለዋወጡ ሰራተኞች እንዲቃረቡ መንገስት መጣር ይገባዋል፡፡
8. መንገድና የምድር ባቡርም ጥቅም ሚሆነው የስራ ማሰልጠኛ የትምህርት ቤቶች በያይነቱ ሲሰራና ማናቸውም እቃ ሁሉ እንደሚቻል መጠን ባገሩ ውስጥ እንዲበጅ መንግስትም ሲጥርበት ነው፡፡
9. መሬቱ በጥቂቶች ሰዎች እጅ የገባ ህዝብ በጣም ይደኸያል፡፡ የባላገሩ ጥቅም እያነሰ ይሄዳል፣ መሬትም ይረክሳል፡፡
10. የመንግስት መሰረት እርሻ ነው፡፡ ባለእርሻ የሚያገኘው ጥቅም ሲያንስ የመንግስት መሰረት አይጠናም፡፡ ባለእርሻ ሺፀቀም ግን መንግስትም ይጠነክራልና ይበረታል፡፡
ነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ ከመቶ አመታት በፊት ያስቀመጧቸው እነዚህ ቁልፍ ቁልፍ ሀሳቦች በአሁኑ ሰአት ብንተገብራቸው ራሱ ብዙ እናተርፋለን፡፡ በጣም መነበብ ያለበት ምርጥ መጽሀፍ ነው፡፡
Report this article
Comments
like
12
Photo of Yonas Asfaw
Like
Comment
Share
Add a comment…
Open Emoji Keyboard
Rukya Hassen Shibeshi
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment