Wednesday, June 19, 2024

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ “ጎሀ ጽባሕ” በተሰኘ መጽሐፍ ምን እያሉን ነው?

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ “ጎሀ ጽባሕ” በተሰኘ መጽሐፍ ምን እያሉን ነው? -ለአማርኛ ሥነ ጽሑፍ እድገትና ለኢትዮጵያ ታሪክ ጥናት ምንጭ ሁነው ሊጠቀሱ የሚችሉ መጻሕፍትን በማበርከት ትልቅ አስተዋጽዖ ያደረጉት ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ (1871-1931 ዓ.ም.) ከብዙ መጻሕፍቶቻቸው መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ 1917 ዓ.ም. የታተመ “ጎሀ ጽባሕ” የተሰኘ መጽሐፍ ነበራቸው፡፡ በቅርቡ በ2014 ዓ.ም. በድጋሚ ታትሟል፡፡ መጽሐፉ በአብዛኛው ሃይማኖታዊ ሥነ ምግባርና ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረግ ማብራሪያ የሚሰጥ መጽሐፍ ነው፡፡ ምናልባት ካላነበቡት በጥንቃቄ ቢያነቡት መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት አንጻር ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ በ“ጎሀ ጽባሕ” መጽሐፍ ምን እያሉን ነው? በማለት ሐሳባቸውን ሙሉ በሙሉ ለመቀበል ጽነት ያላቸውና ከበድ የሚሉ ሐሳቦች አሉበት፡፡ ለምሳሌ ያህል የሚከተሉትን ልጥቀስ 1.) “አዋልድ መጻሕፍት በዓለም ሁሉ በብዙ ተጽፈዋል ከነዚህም የሚበዛው ልብ ወለድ ከቅዱሳት መጻሕፍት ቃል ጋር የማይሰማማ ነው፡፡ አዋልድ መጻሕፍት ማለት በመንፈሳዊ ስለ መላእክትና ስለ ቅዱሳን፣ ስለ ሰማዕታትና መነኮሳት፣ ስለ ሊቃውንትና ስለ ጳጳሳት፣ የተጻፉ የድርሳንና የገድል የክርክርም መጻሕፍት ናቸው፡፡” ( ጎሀ ጽባሕ፣ገጽ 24፣ 2014 ዓ.ም.) -እውነት አብዛኛው አዋልድ መጻሕፍት ልብ ወለድ የሆነ ከቅዱሳት መጻሕፍት ቃል ጋር የማይሰማማ ነው? 2.) “የብሉይና የሐዲስ መጻሕፍት ምሥጢራቸው ባይገለጥልን እንኳን በግድ መቀበል ይገባናል ብለን ከዚህ ቀድሞ አስረድተናል፡፡ የአዋልድን መጻሕፍት ግን የመንፈሳዊም የሥጋዊም ቢሆኑ ወግና ታሪክ ለማወቅ የደራሲውን ደግነትና ክፋት ለመመርመር አንዳንድ ጊዜ ልናነባቸው ይገባል እንጅ እንደ ቅዱሳት መጻሕፍት በግድ ልንቀበላቸው አልታዘዝንም፡፡” (ገጽ 27) -አዋልድን መጻሕፍት በግድ ልንቀበላቸው አይገባንም? አልታዘዝንም? 3.) “ሚስት አግብቶ ልጆች ወልዶ በሥርዐት የሚኖር ከእግዚአብሔር የታዘዘ በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፈ ነውና ሚስት ያላገቡ መነኮሳት ሚስት ታገቡ ሰዎች ይልቅ የበለጠ ክብር ያገኛሉ ብለን በልባችን አናስብም በቃላችንም አንናገርም፡፡” (ገጽ 181) -በክብር በድንግልና የሚኖሩ መነኮሳት በጋብቻ ከሚኖሩት ጋር አይበልጡም? በልባችን ማሰብና በቃላችንም መናገር አይገባንም? 4.) “በእውነተኛ አእምሮ ብንፈርደው ግን ከመነኮሳት ይልቅ ሚስት ያገቡ ሰዎች ሊመሰገኑ ይገባቸዋል፡፡ እነሆ አሁን በጦርነት ጊዜ መመስገን የሚገባው በሰልፉ ጸንቶ የተዋጋ ወታደር ነው እንጅ ሸሽቶ የሄደ ወታደር አይመሰገንም፡፡ እንደዚሁ ሁሉ መንኩሶ በገዳም መኖር ከዚህ ዓለም መከራና ፈተና ሸሽቶ እንደመሄድ ነው፡፡ ሚስት አግብቶ ልጆች ወልዶ በሕገ እግዚአብሔር ጸንቶ የእዚህን ዓለም መከራና ፈተና ታግሦ የሚኖር ሰው ግን በሠይፍ ጸንቶ እንደመዋጋት ነው፡፡” (ገጽ 182) -እውነት ከመነኮሳት ይልቅ ሚስት ያገቡ ሰዎች ሊመሰገኑ ይገባቸዋል? -ምንኩስና በጦርነት ጊዜ ሸሽቶ የሄደ ወታደርን ይመስላል? -ጋብቻን አመስግነው ምንኩስናን ማመስገን ያልፈለጉበትና ያቀረቡት ምሳሌ አግባብነት አለው? 5.) ልብ ብለን ከተመለከትነው በተራ ቁጥር 3 እና 4 ያሉት የብላቴን ሐሳቦች ይጋጫሉ፡፡ ጋብቻና ምንኩስና በክብር አይበላለጡም ካሉ በኋላ እንደገና “የእዚህን ዓለም መከራና ፈተና ታግሦ የሚኖር ሰው ግን በሠይፍ ጸንቶ እንደመዋጋት ነው” በማለት ጋብቻን ከምንኩስና ጋር በማነጻጸር በተራ ቁጥር 4 ላይ ያስበልጡታል፡፡ በጋብቻ የሚኖሩ ሰዎች ከመነኮሳት ይልቅ ሊመሰገኑ ይገባል ይላሉ፡፡ በዚህም ጋብቻን ማስበለጣው ይታወቃል፡፡ 6.) ስለ ሊቃነ ጳጳሳት በሚያብራሩበት የመጽሐፋቸው ክፍል ላይ የሚከተለውን ይላሉ “ኤጲስ ቆጶሳትን … የሚገባቸውን ክብር ልናከብራቸው ይገባል እንጅ ከውኃና ከመንፈስ በጥምቀት የወለዱን አባቶቻችንና አምላኮቻችን ናቸው ለማለት አይገባንም፡፡” (ገጽ 140 ) በገጽ 141 ሐሳባቸውን ለማስረዳት “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ …በምድር ላይ ማንንም አባታችን ብላችሁ አትጥሩ፡፡ አባታችሁ አንዱ በሰማይ ያለው ነውና፡፡ እናንተም ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ ጌቶችም ብላችሁ አትጠሩ፡፡ ጌታችሁም አንዱ ክርስቶስ ነው፡፡” በማለት መንደርደሪያ በማድረግ ያስረዳሉ፡፡ -እውነት ጳጳሳትን አባቶች ማለት አይገባም? -በመጽሐፍ ቅዱስ በሐዋርያት በጻፋት ወንጌልና መልእክታት ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ውጭ አባት፣ ጌታ ያሉት አልነበረም? - እርስዎ በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ሐሳቦች ላይ ምን ይላሉ? ይወያዩበት፡፡ @Yosef Fish

No comments:

Post a Comment