Wednesday, June 19, 2024

🤳 ለልጅ ምክር - ለአባት መታሰቢያ

🤳 ለልጅ ምክር - ለአባት መታሰቢያ ☀️ ልጄ ሆይ! ጠላትህ ሲሞት ወይም ሌላ መከራና ጭንቀት ሲያገኘው ደስ አይበልህ። እርሱ ሞቶ አንተ በዚህ ዓለም አትቀርምና አንተ ደግሞ በሠራኸው ሥራ እንደ እርሱ መከራና ጭንቀት ሳያገኝህ አይቀርም፤ በመከራና በሞትም የሰው ሁሉ ድርሻው ትክክል እንደ ሆነ እወቅ፥ ☀️ ልጄ ሆይ! ነውርህን ለብቻህ የሚነግርህን ሰው አትጥላው፤ አንተም በወዳጅህ ላይ ነውር የሚሆን ነገር ያየህበት እንደ ሆነ ለብቻው አድርገህ ንገረው። ለሌላ ሰው ግን አትንገርበት፥ ☀️ ልጄ ሆይ! በየጊዜው በሰውነትህ ውስጥ የሚነሣውን አሳብ ደግና ክፉ መሆኑን ሳትመረምር ያሰብኸውን ሁሉ ለመፈፀም አትቸኩል፥ ☀️ ልጄ ሆይ! አንተ ራስህ የምትጠቀምበት ወይም ወዳጅህ የሚጠቀምበት ነገር ካልሆነ በቀር "ሰው እንዲያመሰግነኝ" ብለህ ሰውነትህን አታድክም። ሰውም በከንቱ ቢያመሰግንህ ደስ አይበልህ። አመስጋኙም ሁለቱም ይሞታሉና ደስ አይበልህ፥ ☀️ ልጄ ሆይ! በነገርህ ሁሉ የታመንህ ሁን። ባነጋገርህም ደማም ሁን። ሰውን የሚያስፈራና ሰውን የሚያሳዝን ነገር ለመናገር አትድፈር። በልዝብ ምላስ ሰውን አታታል። ሰውንም ከሚየሙ ሰዎች ጋር አትደባለቅ፥ ☀️ ልጄ ሆይ! ንብረትህ በልክ ይሁን። ቤተ ሰዎችም አታብዛ የቀንድ ከብትና የጋማ ከብትም በብዙ አታርባ። ላንተ የማይገባህን ነገር ከማንም ቢሆን አትቀበል። አንተም ለማንም ቢሆን የማይገባውን ነገር አትስጥ፥ ☀️ የማታገኘውን ነገር አትመኝ። ባይንህ ካላየህና እርግጥ መሆኑን ካልተረዳኸው በቀር በማንም ሰው ላይ የሚወራውን ወሬ እውነት ነው ብለህ አትቀበል፥ ☀️ ለሰውነትህ የሚያስፈልገውን ነገር ለማግኘት አስብ እንጂ ሰው የሚጠፋበትን፤ ሰው የሚጨነቅበትን ነገር አታስብ። «ወደጄ ልቤና ሌሎችም - ብላቴን ጌታ ኀሩይ ወ/ስላሴ» ምንጭ፦ ነቢል እንድሪስ #ብላቴን ጌታ ሕሩይ ወልደ ስላሴ "ለልጅ ምክር ለአባት መታሰቢያ" በተሰኘው ድርሳናቸው ልጄ ሆይ እያሉ እንዲህ ይመክሩናል። ልጄ ሆይ፤ የአንበሳና የነብር የሌሎቹንም አራዊት ግርማ ከመፍራት ይልቅ እግዚአብሄርን የማይፈሩ የክፉ ሰዎችን ፊት ፍራ። የዱር አራዊት ለመግደል ካልፈለጓቸው እነርሱ ፈልገው አይመጡም። #ክፉ ሰዎች ግን ሰውን ፈልገው ካላጠፉ እንቅልፍ አይወስዳቸውም ማለፍያ ብዕራቸው ሞገስ ይሁንላቸውና አንጋፋው የብዕር አለቃ ብላቴ ጌታ ህሩይ ወልደ ሥላሴ ለልጅ ምክር አባት መታሰብያ በሚለው መጽሐፋቸው ያሉትን ብንጠቅስ መልካም መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም እንዲህ ይነበባል ልጄ ሆይ ሰው ምንም ብልህና አዋቂ ቢሆን በራሱ ሥራ ብቻ ራሱን ችሎ እንደማይኖር እወቅ ነገር ግን ሁሉም በየሥራው ጸንቶ እርስ በእርሱ ይፈላለጋል ሰውን ሁሉ አክብረህ ኑር ሰውን ሁሉ በሥራው አትናቅ ሥራውንም አትንቀፍ ካሉ በኋላ የሚከተለውን አክለውበታል ገበሬውን አትንቀፍ ከነቀፍከውም እህሉን አትክልቱን ከእርሱ አትፈልግ ወታደሩን አትንቀፍ ከነቀፍከውም ሀገር የሚያጠፋ ነፍስን የሚገድል ጠላት ሲመጣ ተዋጋልኝ አትበል እረኛውን አትንቀፍ ከነቀፍከውም ከብት ጠብቅልኝ ወተት እለብልኝ አትበል ሸክላ ሰሪውን አትንቀፍ ከነቀፍከውም የሸክላ እቃውን አትፈልግ በማለት ይደመድሙታል እንግዲህ ይህ የብላቴ ጌታ ህሩይ መጽሐፍ አደባባይ የዋለው ምንአልባት ከዛሬ ሰማንያ ዓመት በፊት ነው እኛ ግን እነዚያን እርሳቸው አትንቀፍ ያሏቸውን ዛሬም እየነቀፍን እንታያለን ነቅፈንም ለሌላ ነቃፊ እየሰጠን የስድብ ባላደራዎች ሆነን ለወገን የሚበጀውን እየተውን ለወገን የማይበጀውን ኢትዮጵያችንን የሚያለማትን እየተቃወምን ኢትዮጵያችንን የሚያጠፋትን እየደገፍን እንገኛለን ይህን ታድያ ምን ይሉታል ሲሉ መጽሐፉን ያነበቡ አስተያየት ሰጪ አክለው ተናገሩ

No comments:

Post a Comment