Wednesday, April 21, 2021

1) በሕግ እና በጸጋ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው ?

እንግዲህ በዚህ ውስጥ ያለውን የፀጋና የህግን ልዩነት ምን እንደሆነ እንደ እግዚአብሄር ቃል ማየት ያስፈልገናል:: በመጀመሪያ ደረጃ ሕግን ስናየው እግዚአብሄር ሕግን በሙሴ አማካኝነት ለእስራኤል ሕዝብ የሰጣቸው ስጋቸውን የሚገዙበት የሕግ ስርአት ነበር:: ይህም ማለት ሰው ሁሉ በአዳም በደል አማካኝነት ኃጢያት ወደ ሰው ሁሉ ስለገባ ማንኛውም ሰው በመንፈሱ የሞተ ስለሆነ ወደ እግዚአብሄር መቅረብ አይቻልም ነበር:: ስለዚህ እግዚአብሄር ለእስራኤል ሕዝብ የሕግን ስርአት ሰጣቸው::

    ይህም ሕግ ሰዎችን ለጊዜውም ቢሆን በምድር ሲመላለሱ ራሳቸው በስጋቸው ኃጥያትን እንዳይፈፅሙና ስጋቸውን በኃጢያት እንዳያቆሽሹ የተሰጣቸው የሕግ ስርአት ነበር:: ኃጢያት እንኳን ቢሰሩ ስጋቸውን ብቻ ሊያነፁበት የሚችል የሕግ ስርአት ተሰቷቸው ነበር:: ልብ ማለት ያለብን ይህ የተሰጣቸው ሕግ የስጋ ኃጢያታቸውን ብቻ ነበር ማንፃት የሚችለው:: ነፍሳችንን የማንፃት ኃይል ግን አልነበረውም:: ስለዚህ እስራኤሎች ዕለት በዕለት ለሰሩት ኃጢያት ስጋቸውን ብቻ የሚያነፁበት የሕግ ስርአት ተሰጥቷቸው ነበር::

''ይህም ለአሁኑ ጊዜ ምሳሌ ነው እንደዚህም መባና መስዋዕት ይቀርባሉ እነዚህም እስከመታደስ ዘመን ድረስ የተደረጉ ስለ ምግብና ስለ መጠጥም ስለ ልዩ ልዩ መታጠብም የሚሆኑ የስጋ ስርአቶች ብቻ ናቸውናየሚያመልከውን በሕሊና ፍፁም ሊያደርጉት አይችሉም::'' (ዕብ 9_10)

    ብሎ የእግዚአብሄር ቃል የስጋ ስርአት ብቻ እንደነበር አስረግጦ ያስተምረናል:: ይህም ማለት ያ የሕግ ስርአት ስጋን የማንፃት ኃይል ብቻ ነበረው እንጂ ሕሊናችንን የማንፃት ኃይል አልነበረውም::

የኮርማዎችና የፍየሎች ደም በረከሱትም ላይ የተረጨ የጊደር አመድ ሥጋን ለማንፃት የሚቀድሱን ከሆኑ ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሄር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያው እግዚአብሄርን ልታመልኩ ከሞተ ስራ ሕሊናችሁን ያነፃ ይሆን ?'' (ዕብ 9:13-14) ስለዚህ ያ ሕግ ስጋን ብቻ የማንፃት ኃይል ነበረው እንጂ ከአዳም የተላለፈብንን የዘር ኃጢያት የማንፃት ጉልበት አልነበረውም:: ስለዚህ ሕግ ለስጋችን ኃጢያት ማንፃት ቢሰጥም ማለትም ማንም ሰው ከሕግ ኃጢያት መንፃት ቢችልም በሙሴ በኩል የተሰጠው የሕግ ስርአት በአዳም አማካኝነት የተላለፈብንን ኃጢያት ማንፃት ስለማይችል ፀጋ መምጣቱ አስፈላጊ ሆነ::

    ፀጋ ማንም በጉልበቱ እንዳገኘው ሊመፃደቅ እንዳይችል በምድር ላይ ስራችንን ሁሉ ሰርቶ ከአዳም ኃጢያት ነፃ የወጣነው በኢየሱስ ስራ ብቻ መሆኑን ማወቅ ነው::
    ''እንግዲህ በስጋ አባታችን የሆነ አብርሀም ምን አገኘ እንላለን ? አብርሀም በስራ ፀድቆ ቢሆን የሚመካበት አለውና ነገር ግን በእግዚአብሄር ዘንድ አይደለም::"" (ሮሜ 4:1)

እንግዲህ ቃሉ እንደሚለን አብርሀም በስራ ቢሆን ኖሮ የፀደቀው የሚመካው በእግዚአብሄር ሳይሆን በራሱ እንደሆነ የእግዚአብሄር ቃል ያስተምረናል:: እንግዲህ ይህ መመፃደቅ እንዳይኖር መዳን በእኛ መልፋት ሳይሆን በክርስቶስ ስራ እኛ እንዲሁ በነፃ በማመን ብቻ እንድናለን::

    ''ለሚሰራ ደመወዝ እንደ እዳ ነው እንጂ እንደ ፀጋ አይቆጠርለትም ነገር ግን ለማይሰራ ኃጢያተኛውንም በሚያፀድቅ ለሚያምን ሰው እምነቱ ፅድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል::'' (ሮሜ 4:4-6)

ቃሉ እንደሚለው በስራችን ሳይሆን ስራችንን ሁሉ በሰራልን በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል እኛ እንዲሁ በፀጋው እንድናለን::


    ስለዚህ ፀጋ ሙሉ ለሙሉ እግዚአብሄርን የምናመልክበትን ሕሊናችንን አንፅቶ ፃድቅ ለመባል ሲያበቃን የሕግ ስርአት ግን ስጋን የማንፃት ኃይል እንጂ ያለው ሕሊናችንን አንፅቶ ፃድቅ ሊያስብለን አይችልም:: ለዚህም ነው በብሉይ ኪዳን ውስጥ አንድም ሰው ቅዱስ ይባላል እንጂ ፃድቅ ተብሎ አይጠራም ነበር:: ስለዚህ በክርስቶስ በኩል ያገኘነው የፀጋ ስጦታ ወደ እግዚአብሄር መንግስት የሚያስገባ ሲሆን ሕግ ግን በምድር ሳለን በስጋችን ረጅም እድሜ ለመኖር የተሰጠ የሕግ ስርአት ነው:: ይህም ማለቴ ሕግ አያስፈልግም ማለቴ ሳይሆን ሕግ ባሁን ሰዓት ከእምነት በኋላ የሚደረግ ነው:: የሕግ ስራ በአዳም በኩል የተላለፈብንን የዘር ኃጢያት የማስወገድ ኃይል የለውም:: ፀጋ ግን ከአዳም የተላለፈብንንም ሆነ በሕግ ያደረግነውንም ኃጥያት የማንፃት ኃይል አለው:: ይህም ማለት ማንም ሰው ከፀጋ በፊት በሕግ ስራ መፅደቅ አይችልም::

No comments:

Post a Comment